ዮናስ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ዮናስ ከእግዚአብሔር ለመሸሽ ሞከረ 1 የጌታ ቃል ወደ አሚታይ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “ተነሥ፥ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋታቸው በፊቴ ወጥቶአልና።” 3 ዮናስ ግን ከጌታ ፊት ወደ ተርሴስ ለመሸሽ ተነሣ፤ ወደ ያፎም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምትሄድ መርከብ አገኘ፤ ከጌታ ፊት ሸሽቶ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ለመሄድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ ገባ። 4 ጌታ ግን በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አስነሣ፥ በባሕሩም ላይ ታላቅ ማዕበል ተነሣ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። 5 መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱ እንዲቀልልላቸውም መርከቢቱ ውስጥ የነበሩትን ዕቃዎች ወደ ባሕር ጣሉ፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ታችኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር። 6 የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ “እንዴት ትተኛለህ? ተነሥ አምላክህን ጥራ፥ ምናልባትም እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን ይሆናል” አለው። 7 እርስ በእርሳቸውም፦ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደመጣብን እንድናውቅ ኑ፥ ዕጣ እንጣጣል” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፥ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ። 8 እንዲህም አሉት፦ “እባክህ ንገረን፥ ይህ ክፉ ነገር በምን ምክንያት መጣብን? ሥራህ ምንድነው? ከወዴት መጣህ? አገርህስ የት ነው? የየትኛው ሕዝብ ወገን ነህ?” 9 እርሱም፦ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፥ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን፥ የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ” አላቸው። 10 ሰዎቹም እጅግ ፈሩ፥ እንዲህም አሉት፦ “ይህ ያደረግኸው ምንድነው?” እርሱ ስለ ነገራቸው፥ ከጌታ ፊት እንደ ኰበለለ አውቀዋልና። 11 እንዲህም አሉት፦ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን ምን እናድርግብህ?” ባሕሩ መናወጡን ቀጥሎ ነበርና። 12 እርሱም፦ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደመጣባችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው። 13 ሰዎቹ ወደ የብሱ ሊመለሱ አጥብቀው ቀዘፉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፥ ባሕሩ በማዕበሉ ይናወጥባቸው ነበርና። 14 ስለዚህ ወደ ጌታ ጮኹ፥ እንዲህም አሉ፦ “ጌታ ሆይ! እባክህ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ እንለምንሃለን፥ ንጹሕንም ደም በእኛ ላይ አታድርግ፤ ጌታ ሆይ ደስ የሚያሰኝህን አድርገሃልና።” 15 ዮናስንም አንሥተው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም መናወጡን አቆመ። 16 ሰዎቹም ጌታን እጅግ ፈሩ፥ ለጌታም መሥዋዕትን ሠዉ፥ ስእለትንም ተሳሉ። |