ኢዮብ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 “የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ቀኖቹ እንደ ምንደኛ ቀኖች አይደሉምን? 2 አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ 3 እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። 4 በተኛሁ ጊዜ፦ መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪ ነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። 5 ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፥ ቆዳዬ ያፈከፍካል እንደገናም ይመግላል። 6 ቀኖቼ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኩላሉ፥ ያለ ተስፋም ያልቃሉ።” 7 “ሕይወቴ እስትንፋስ እንደሆነ አስታውስ፥ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። 8 የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፥ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም። 9 ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም። 10 ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።” 11 “ስለዚህም ከመናገር አፌን አልከለክልም፥ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፥ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጉራለሁ። 12 እኔ ባሕር ነኝ ወይስ ዓሣ አንበሪ? ባላዬ ጠባቂ የምታኖርብኝ? 13 እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጉርጉሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ 14 አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፥ 15 ከዚህ ሥጋ ይልቅ ነፍሴ መታነቅንና ሞትን መረጠች። 16 ሕይወቴን ናቅኋት፥ ለዘለዓለም ልኖር አልወድድም፥ ቀኖቼ እስትንፋስ ናቸውና ተወኝ። 17 ሰው ምንድነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ 18 ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? 19 የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? 20 ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደሆነ ምን ላድርግልህ? ስለምን እኔን ዒላማ አደረግኸኝ? ስለምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? 21 ስለምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፥ ትፈልገኛለህ፥ እኔ ግን የለሁም።” |