Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 39 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን?

2 ከእርሷ የሚወስዱባትንስ ወራት መቁጠር ትችላለህን? የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?

3 ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥ ከምጣቸውም ያርፋሉ።

4 ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥ በሜዳም ያድጋሉ፥ ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም።

5 የሜዳውንስ አህያ ማን ነፃ ለቀቀው? የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው?

6 በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፥ መኖሪያውም በጨው ምድር ነው።

7 በከተማ ውካታ ይስቃል፥ የነጂውን ጩኸት አይሰማም።

8 ተራራውን እንደ መሰማርያው ይቃኘዋል፥ ለምለሙንም ሣር በሙሉ ይፈልጋል።

9 ጐሽ ሊያገለግልህ ፈቃደኛ ነውን? ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን?

10 ጐሽ እንዲተልምልህ ልታጠምደው ትችላለህን? ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጉላልን?

11 ጉልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ በእርሱ ትታመናለህን? አድካሚ ሥራህን ለእርሱ ትተዋለህን?

12 ወደ አንተ እንደሚመለስና፥ ሰብልህንስ በአውድማህስ እንደሚያከማችልህ ትተማመናለህን?

13 ምንም እንኳን እንደ ሸመላ ባትበርም፥ የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፤

14 እንቁላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥ በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፥

15 እግር ሊሰብረው እንደሚችል፥ የምድረ በዳም አውሬ ሊረግጠው እንደሚችል ትረሳለች።

16 የእርሷ ያልሆኑ ይመስል በልጆችዋ ትጨክናለች፥ ድካምዋ ከንቱም ሊሆን ቢችልም አትፈራም፥

17 እግዚአብሔር ጥበብን ነሥቷታልና፥ ማስተዋልንም አላደላትምና።

18 ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች።

19 ለፈረስ ጉልበቱን ትሰጠዋለህን? አንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን?

20 እንደ አንበጣስ ታፈናጥረዋለህን? ግርማዊ ማንኰራፋቱ እጅግ ያስፈራል።

21 በሸለቆው ውስጥ በኮቴው ይጐደፍራል፥ በጉልበቱም ደስ ይለዋል፥ ሰይፍ የታጠቁትንም ለመጋፈጥ ይወጣል።

22 በፍርሃት ላይ ይስቃል፥ በጭራሽ አይደነግጥም፥ ሰይፍም አያሸሸውም።

23 በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆ፥ የሚብለጨልጭ ጦርና ሰላጢን ያንኳኳሉ።

24 በነውጥና በቁጣ መሬትን ይውጣል፥ የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም።

25 የመለከትም ድምፅ ሲሰማ፦ እሰይ! ይላል፥ ከሩቅ ሆኖ የሠራዊቱን ውካታ፥ ፍልምያውንና የአለቆቹን ጩኸት፥ ያሸታል።

26 በውኑ ጭልፊት የሚያንዣብበው፥ ክንፎቹንስ ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ጥበብ ነውን?

27 ንስር ከፍ ከፍ የሚለው፥ ቤቱንም በከፍታ ላይ የሚያደርገው በአንተ ተእዛዝ ነውን?

28 የሌሊት መኖርያው ዓለት ነው፥ የዓለት ጫፍም መከላከያ ይሆነዋል።

29 በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፥ ዐይኖቹም ከሩቅ ይመለከታሉ።

30 ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፥ በድን ባለበትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos