Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 36 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ኤሊሁም ቀጠለ፤ እንዲህም አለ፦

2 “ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ።

3 እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥ ፈጣሪዬም ጻድቅ መሆኑን አሳይሃለሁ።

4 ቃሌ በእውነት ሐሰት የለበትም፥ በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ።

5 እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፥ እርሱም በጥበባዊ ኃይሉም ጽኑ ነው።

6 እርሱ በደለኛን በሕይወት አይጠብቅም፥ ለችግረኞች ግን ይፈርዳል።

7 ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፥ ለዘለዓለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ።

8 በሰንሰለት ቢታሰሩ፥ ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥

9 ተግባራቸውንና መተላለፋቸውን በትዕቢትም እንደሚሠሩም ይናገራቸዋል።

10 ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥ ከክፋትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል።

11 ከሰሙትና ካገለገሉት፥ ዕድሜአቸውን በብልጽግና፥ ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ።

12 ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥ ያለ እውቀትም ይሞታሉ።

13 ልበ ደንዳኖች ግን ቁጣን ይወዳሉ፥ እርሱም ባሠራቸው ጊዜ አይጮኹም።

14 በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥ ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል።

15 የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፥ በመከራም እንዲሱሙ ያደርጋቸዋል።

16 እንዲሁም አንተን ከመከራ ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥ በማዕድህም ላይ ቅባት የሞላበት ምግብ በተዘጋጀ ነበር።

17 አንተ ግን የበደለኞች ፍርድ ደረሰብህ፥ ፍርድና ብይን እንደሚይዛቸው።

18 ሀብት ወደ ስድብ አስቶ እንዳይወስድህ፥ ትልቅ ጉቦም ከመስመር እንዳያስወጣህ።

19 ብልጽግናህና ኃይልህ በሙሉ ከችግር የሚጠብቅህ ይመስልሃልን?

20 ሰዎች ድንገት የሚሞቱበትን ሌሊትን አትመኛት።

21 አሁን ከመከራ የምትፈተነው ለዚሁ ነውና፥ ወደ በደል እንዳትመለስ ተጠንቀቅ።

22 እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ልዑል ነው፥ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው?

23 ማነው መንገዱን የሚያሳየው? ወይስ፦ ‘ተሳስተሃል’ የሚለው ማን ነው?

24 ይልቁንም ሰዎች የዘመሩለትን ሥራውን ማክበርን አስታውስ።

25 ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፥ ሰውም ከሩቅ ያየዋል።

26 እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።

27 የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፥

28 ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በገፍ ያፈሳሉ።

29 የደመናውንም መዘርጋት፥ የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው?

30 እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፥ የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል።

31 በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፥ ብዙም ምግብ ይሰጣል።

32 መብረቅን በእጆቹ ይይዛል፥ ያዘዘውንም እንዲመታ ያደርገዋል፥

33 የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፥ እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos