ኢዮብ 30 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 “አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥ አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥ በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ። 2 የቀድሞ ጥንካሬአቸው ጠፍቶ ነበርና የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል? 3 በችግርና በራብ መንምነው፥ በፈረሰውንና በተተወው የጨለመ ምድረ በዳን ሥራ ሥሮችን ያኝካሉ። 4 በቁጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን ቅጠላ ቅጠል ይቀጥፋሉ፥ እንዲሞቃቸውም የክትክታ ሥር ይበላሉ። 5 ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፥ በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል። 6 በሸለቆ ጉድጓድ፥ በምድርና በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ። 7 በጫካ ውስጥ ይጮኻሉ፥ ከቁጥቋጦ በታች ተሰብስበዋል። 8 የአላዋቂና የነውረኞች ልጆች ናቸው፥ ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው።” 9 “አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው። 10 ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፥ አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም። 11 የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፥ እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል። 12 በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥ እግሬንም ያሰናክላሉ፥ የጥፋታቸውን መንገዶች በእኔ ላይ ይቀይሳሉ። 13 ጐዳናዬን ያበላሻሉ፥ ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ። 14 በሰፊው መከላከያን ጥሰው እንደሚመጡ ይመጡብኛል፥ በፍርስራሽ ውስጥ ይንከባለላሉ። 15 ድንጋጤ በላዬ ተመለሰብኝ፥ ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱታል፥ ብልጽግናዬም እንደ ደመና አልፋለች።” 16 “እነሆ ሕይወቴ እያለቀች ነው፥ የመከራም ዘመን ያዘኝ። 17 የሌሊቱ ስቃይ እስከ አጥንቶቼ ድረስ ይዘልቃል፥ ሁለመናዬንም ስለሚበላኝ ጅማቶቼ አያርፉም። 18 ከሕመሜ ብርታት የተነሣ ልብሴ ተበላሸ፥ እንደ ቀሚስ ክሳድ ያንቀኛል። 19 በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ። 20 ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፥ ተነሣሁ፥ ነገር ግን ዝም ብለህ ተመለከትኸኝ። 21 ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፥ በጠንካራ እጅህም አሰቃየኸኝ። 22 በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስጋለብከኝ፥ በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ። 23 ለሞት፥ ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና።” 24 “ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጅ አይዘረጋምን? በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን? 25 ለተጨነቁት አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን? 26 ነገር ግን በጎነትን ስጠባበቅ ክፉ ነገር መጣብኝ፥ ብርሃንን ተስፋ ሳደርግ ጨለማ መጣ። 27 አንጀቴ ተናወጠ፥ አላረፈምም፥ የመከራም ዘመን መጣብኝ። 28 በፀሐይ ሳይሆን በትካዜ ጠቁሬ ሄድሁ፥ በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ። 29 ለቀበሮ ወንድም፥ ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ። 30 ቆዳዬ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፥ አጥንቴም ከትኩሳት የተነሣ ተቃጠለ። 31 ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥ እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ መሳርያ ሆነ።” |