ኢዮብ 29 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ኢዮብም ንግግሩን ቀጠለ፤ እንዲህም አለ፦ 2 “እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደነበረው ጊዜ፥ እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ! 3 በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥ 4 ብርቱ እንደ ነበርኩበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ድንኳኔን ይጠብቅ በነበረበት ጊዜ፥ 5 ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥ 6 መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ዓለቱ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ። 7 ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥ 8 ወጣቶች እኔን አይተው ይሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ይቆሙ ነበር። 9 መኮንኖች ከመናገር ዝም ይሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር። 10 የታላላቅ ሰዎች ድምፅ ይደበቅ፥ ምላሳቸውም ከትናጋቸው ጋር ይጣጋ ነበር። 11 የሰማችኝ ጆሮ ታሞግሰኝ፥ ያየችኝም ዐይን ትመሰክርልኝ ነበር፥ 12 የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ወላጅ አልባውንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና። 13 ለሞት የቀረበው ሰው በረከት በላዬ ይደርስ ነበር፥ የመበለቲቱንም ልብ እልል አሰኝ ነበር። 14 ጽድቅን ለበስሁ እርሷም ለበሰችኝ፥ ፍርዴም እንደ ካባና እንደ ቆብ ነበረ። 15 ለዐይነ ስውር ዐይን፥ መሄድ ለተሳነው እግር ነበርሁ። 16 ለድሀው አባት ነበርሁ፥ ለማላውቀውም ሰው ጠበቃ ነበርሁ። 17 የግፈኛውን መንጋጋ እሰብር፥ የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጥል ነበር። 18 እኔም፦ ‘በልጆቼ መካከል በክብር እሞታለሁ፥ ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፥’ እል ነበር፤ 19 ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግተው፥ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድር ነበር፤ 20 ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶ፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞ ነበር። 21 ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ። 22 ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፥ ንግግሬም በእነርሱ ላይ ተንጠባጠበ። 23 ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፥ የበልግን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ። 24 እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፥ የፊቴም ብርሃን አበረታታቸው። 25 መንገዳቸውን መረጥሁ፥ እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፥ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ ኀዘንተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።” |