Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “ሁሉን የሚችል አምላክ የወሰናቸውን ጊዜያት ለምን አያሳውቅም? የሚያውቁትስ ቀኖቹን ለምን አያዩም?

2 የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፥ መንጋዎቹን ቀምተው ያሰማራሉ።

3 የወላጅ አልባውን አህያ ይነዳሉ፥ የመበለቲቱን በሬ ለመያዣነት ይወስዳሉ።

4 ድሆቹን ከመንገድ ያስወጣሉ፥ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ።

5 እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፥ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል።

6 እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፥ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ።

7 ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ የሚደረብ የላቸውም።

8 ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፥ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ።

9 አባቱ የሞተበትን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ፥ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ።

10 ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፥ ተርበው ነዶዎችን ይሸከማሉ፥

11 በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያወጣሉ፥ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ።

12 በከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ያቃስታሉ፥ ቁስለኞችም ለእርዳታ ይጮኻሉ፥ እግዚአብሔር ግን ልመናቸውን አይመለከትም።”

13 “እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፥ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም።

14 ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፥ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፥ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው።

15 የአመንዝራ ሰው ዐይን ጨለማን ይጠብቃል፦ የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል።

16 ቤቶቹን በጨለማ ይሰረስራሉ፥ በቀን ይሸሸጋሉ፥ ብርሃንም አያውቁም።

17 የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፥ የሞትን ጥላ አስደንጋጭነት ያውቃሉና።”

18 “እነርሱ በውኃ ላይ ተንሳፈው ያልፋሉ፥ ድርሻቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፥ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይመለሱም።

19 ድርቅና ሙቀት የበረዶውን ውኃ ያጠፋሉ፥ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች።

20 ማኅፀን ትረሳዋለች፥ ትልም በደስታ ይጠባዋል፥ ዳግመኛም የሚያስታውሰው የለም፥ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።”

21 “የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፥ ለመበለቲቱም መልካም አያደርግም።

22 ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ያስቀጥላል፥ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም።

23 እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፥ ዐይኖቹ ግን መንገዳቸውን ይመለከታሉ።

24 ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፥ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፥ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፥ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ።

25 እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ከንቱ የሚያደርገው ማን ነው?”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos