Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦

2 “ዛሬም ደግሞ የኀዘን እንጉርጉሮዬ ገና መራራ ነው፥ በመቃተት ብጮኽም እጁ በእኔ ላይ እንደ ከበደች ናት።

3 እርሱን እንዴት እንደማገኘው ምነው ባወቅሁ! ወደ ተቀመጠበትስ ስፍራ ምነው በደረስሁ!

4 በፊቱ አቤቱታዬን አቀርብ ነበር፥ አፌንም በማስረጃ እሞላው ነበር።

5 የሚመልስልኝም ቃል ምን እንደሆነ አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም አስተውል ነበር።

6 በታላቅ ኃይሉ ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን? ይልቁንም! ማዳመጥ ይበቃው ነበር።

7 የሚከራከረው ቅን ሰው መሆኑን ይመሰክር ነበር፥ እኔም በፈራጅ ፊት ለዘለዓለም ነፃ እወጣ ነበር።”

8 “እነሆ፥ ወደፊትም ብሄድ፥ እርሱ የለም፥ ወደ ኋላም ብሄድ፥ አላየውም፥

9 ወደሚሠራበት ወደ ግራ ብሄድ አይታየኝም፥ በቀኜም ይሰወራል፥ አላየውምም፥

10 የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፥ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ።

11 እግሬ ዱካውን ተከትሎአል፥ መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ከመስመር አልወጣሁም።

12 ከተናገራቸው ትእዛዛት አልኮበለልኩም፥ የአፉን ቃል በልቤ ደብቄአለሁ።

13 እርሱ ግን የሚተካከለው የለውም፥ ማንስ ውሳኔውን ያስቀይረዋል? የወደደውንም ያደርጋል።

14 በእኔ ላይ የወሰነውን ይፈጽማል፥ እንደዚህ ያሉ ብዙ ብያኔዎች እንዳሉት።

15 ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፥ ባሰብሁም መጠን ፈራሁት።

16 እግዚአብሔር ልቤን አባብቶታልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል።

17 በጨለማው አልተደመሰስኩም፥ ነገር ግን ድቅድቁ ጨለማ ፊቴን ሸፈነ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos