ኢዮብ 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ 2 “ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፥ ይህም እንደ ማጽናናት ይቆጠርላችሁ። 3 እናገር ዘንድ ተውኝ፥ ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ። 4 በውኑ የኀዘን እንጉርጉሮዬን ለሰው እናገራለሁን? አለመታገሤ ተገቢ አይደለምን? 5 ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፥ እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ። 6 እኔ ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፥ ሰውነቴንም መንቀጥቀጥ ይይዘዋል። 7 ስለምን ክፉዎች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? ኃይላቸውንስ ስለምን ያጠነክራሉ? 8 ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው። 9 ቤታቸው በሰላም ከፍርሃት ነጻ ነው፥ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም። 10 ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፥ ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም። 11 ሕፃኖቻቸውን እንደ መንጋ ይለቃሉ፥ ልጆቻቸውም ይቧርቃሉ። 12 ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥ በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል። 13 ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፥ በሰላምም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።” 14 እግዚአብሔርንም፦ “ከእኛ ዘንድ ራቅ፥ መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም። 15 እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው? ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል?” ይላሉ። 16 “እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን? የክፉዎች ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።” 17 “የክፉዎች መብራት የጠፋው፥ መቅሠፍትም የመጣባቸው፥ እግዚአብሔርም በቁጣው መከራ የከፈላቸው፥ 18 በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?” 19 እናንተ፦ “እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል” ብላችኋል። ይልቁንም እራሳቸው ይረዱት ዘንድ ፍዳን ይክፈላቸው። 20 ዐይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥ ሁሉን ከሚችል አምላክ ቁጣ ይጠጡ። 21 የወራታቸውስ ቍጥር ከተቈረጠ፥ ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል? 22 ከፍ ከፍ ባሉት ላይ ለሚፈርደው እግዚአብሔር ሰው እውቀትን ሊያስተም ይችላልን? 23 አንድ ሰው በሰላም ተረጋግቶ ሲቀመጥ ከነሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል። 24 በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥ የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል። 25 ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ በተመረረች ነፍስ ይሞታል። 26 በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥ ትልም ይከድናቸዋል። 27 “እነሆ፥ ሐሳባችሁን፥ የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ። 28 እናንተ፦ የከበርቴው ቤት የት ነው? ክፉዎች ያደሩበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል። 29 መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን? ምስክርነታቸውንስ አትረዱምን? 30 ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚተርፍ፥ በቁጣው ቀን እንደሚድን። 31 ስለ መንገዱ ፊቱ ለፊት የሚወቅሰው ማን ነው? ስለ ሠራውስ የሚቀጣው ማን ነው? 32 እርሱን ግን ለቀብር ይሸከሙታል፥ መቃብሩም ይጠበቃል። 33 የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፥ በኋላውም ሰው ሁሉ ይከተለዋል፥ በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ። 34 የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?” |