Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ልጆች በጌታ ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በጌታ ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ።

2 ጌታም ሰይጣንን፦ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፦ “በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርሷም ተመላለስሁ” ብሎ ለጌታ መለሰ።

3 ጌታም ሰይጣንን፦ “በውኑ አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፥ ያለ ምክንያት ይጠፋ ዘንድ በእርሱ ላይ ብትገፋፋኝም እንኳን፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ጠብቋል።”

4 ሰይጣንም መልሶ ጌታን እንዲህ አለው፦ “በቆዳ ላይ ቆዳ፥ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል።

5 ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።”

6 ጌታም ሰይጣንን፦ “ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው” አለው።

7 ሰይጣንም ከጌታ ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ መርገጫ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው።

8 ኢዮብም ሥጋውን ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።

9 ሚስቱም፦ “እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው።

10 እርሱ ግን፦ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፥ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።

11 ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፥ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው ቢልዳድ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ።

12 ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፤ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፥ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ።

13 ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፥ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተው ነበርና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos