ኢዮብ 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ 2 “ነፍሴን የምትነዘንዙት፥ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው? 3 ይኸው ስትሰድቡኝ ዐሥር ጊዜ ነው፥ ስታሰቃዩኝም አላፈራችሁም። 4 በእውነትም የሳትሁ እንደሆነ፥ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች። 5 በእውነትም ብትኩራሩብኝ፥ በመዋረዴም ብታሳብቡ፥ 6 እንግዲህ እግዚአብሔር ጥፋተኛ እንዳደረገኝ፥ በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ። 7 እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፥ ድረሱልኝ ብዬ ብጣራ ፍርድ የለኝም። 8 እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥ በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል። 9 ክብሬን ገፈፈኝ፥ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ። 10 በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፥ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፥ 11 ቁጣውንም አነደደብኝ፥ እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ። 12 ሠራዊቱ አብረው መጡ፥ መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥ በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።” 13 “ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥ የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ። 14 ዘመዶቼ ተቋረጡ፥ ወዳጆቼም ረሱኝ። 15 እንግዶቼ በቤቴ፥ ሴቶች አገልጋዮቼም እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፥ በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ። 16 አገልጋዬን ብጠራ አይመልስልኝም፥ በአፌም መለማመጥ አለብኝ። 17 ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥ የእናቴም ማኅፀን ልጆች ተጸየፉኝ። 18 ሕፃናት እንኳ አጠቁኝ፥ ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ። 19 አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፥ እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ። 20 አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፥ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ። 21 እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ራሩልኝ፥ ራሩልኝ፥ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና። 22 ስለምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለምን አትጠግቡም?” 23 “ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! 24 ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘለዓለም ቢቀረጽ! 25 እኔን ግን የሚቤዥኝ ሕያው እንደሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንደሚቆም፥ 26 ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማይ አውቃለሁ። 27 እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዐይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። 28 በእውነት፦ እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ 29 ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቁጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።” |