ኢዮብ 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “እስከ መቼ ቃላትን ታበዛለህ? አስተውል፥ ከዚያም እኛ እንናገራለን። 3 ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን? ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ቀለልን? 4 ቁጣ ወርሶሃል፥ ስለ አንተ ሲባል፥ ምድር ባድማ ትሆናለችን? ወይስ ዓለት ከስፋራው ይነቀላልን?” 5 “የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም። 6 ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥ መብራቱም በላዩ ይጠፋል። 7 የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ ምክሩም ትጥለዋለች። 8 እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥ በመረብም ላይ ይሄዳል። 9 አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥ ወጥመድም ይበረታበታል። 10 በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥ በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች። 11 ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥ በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች። 12 ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥ መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል። 13 የሰውነቱ ክፍሎች ይጠፋሉ፥ የሞትም የበኩር ልጅ ሰውነቱን ይበላል። 14 ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፥ ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኩሉታል። 15 በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፥ በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል። 16 ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥ ጫፉም ከበላይ ይረግፋል። 17 መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥ በሜዳም ስም አይቀርለትም። 18 ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥ ከዓለምም ያሳድዱታል። 19 ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፥ በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም። 20 የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥ እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ። 21 በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥ እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው።” |