ኢዮብ 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 መንፈሴ ደከመ፥ ቀኖቼ አለቁ፥ መቃብርም ተዘጋጅቶልኛል። 2 አላጋጮች በእኔ ዘንድ አሉ፥ ዓይኔም ማስቈጣታቸውን ትመለከታለች። 3 “እባክህን፥ አንተ ዋስ ሁነኝ፥ ለእኔ ተያዥ የሚሆነኝ ማን ነው? 4 ልባቸውም እንዳያስተውል ከልክለኸዋል፥ ስለዚህ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም። 5 ለብዝበዛ ባልንጀሮቹን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው፥ የልጆቹ ዐይን ይጨልማል።” 6 “ለሕዝብም ምሳሌ አደረገኝ፥ በፊቱ ላይ እንደሚተፉበት ሰው ሆንሁ። 7 ዓይኔም ከኀዘን የተነሣ ፈዘዘች፥ መላ ሰውነቴ እንደ ጥላ ሆነ። 8 ቅኖች ሰዎች በዚህ ነገር ይረበሻሉ፥ ንጹሕም አምላኩን በሚክድ ላይ ይበሳጫል። 9 ጻድቅ ግን መንገዱን ያጠነክራል፥ እጁም ንጹሕ የሆነ ሰው ኃይልን እየጨመረ ይሄዳል። 10 ነገር ግን እናንተ ሁሉ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ፥ በእናንተም ዘንድ ጠቢብ አላገኝም። 11 ቀኖቼ አለፉ፥ ዕቅዴና የልቤ ምኞት ቀለጠ። 12 ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፥ ብርሃኑም ወደ ጨለማ የቀረበ ይመስላቸዋል። 13 ተስፋ ባደርግ ሲኦል ቤቴ ናት፥ ምንጣፌንም በጨለማ ዘርግቻለሁ። 14 መበስበስን፦ አንተ አባቴ ነህ፥ ትልንም፦ አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ። 15 እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይ ማን ነው? 16 ወደ ሲኦል ይወርዳልን? አብረን ወደ አፍር ውስጥ እንገባ የለምን?” |