Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፥ ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው።

2 እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፥ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።

3 ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ።

4 እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፥ ሁላችሁም የማትጠቅሙ ሐኪሞች ናችሁ።

5 ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ! ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።

6 አሁንም ክርክሬን ስሙ፥ የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ።

7 በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን? ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን?

8 ለእርሱ እያዳላችሁ ነውን? ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን?

9 ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን? ወይስ በሰውን እንደምታታልሉ ልታታልሉት ትፈልጋላችሁን?

10 በስውር ብታዳሉ በጥብቅ ይገሥጻችኋል።

11 ክብሩስ አያስፈራችሁምን? ግርማውስ አይወድቅባችሁምን?

12 ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፥ ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው።”

13 “ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፥ የፈለገ ነገር ይምጣብኝ።

14 ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ።

15 እነሆ፥ ሊገድለኝ ይችላል፥ ተስፋም ባይኖረኝ፥ ነገር ግን ስለ መንገዴ በፊቱ እሟገታለሁ።

16 ክፉ ሰው በፊቱ አይቀርብምና፥ እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል።

17 ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥ ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ።

18 እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ። ጽድቄም እንደሚገለጽ አውቃለሁ።

19 ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው? አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ።

20 ነገር ግን ሁለት ነገሮችን አድርግልኝና፥ የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፥

21 እጅህን ከእኔ አርቅ፥ ግርማህም አታስደንግጠኝ።

22 ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ። ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ።

23 ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው? መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ።

24 ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ለምንድነው?

25 የረገፈውን ቅጠል ታስደነግጣለህን? ወይስ የደረቀውን ገለባ ታሳድዳለህን?

26 የመረረ ነገር ጽፈሕብኛልና፥ የልጅነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ።

27 እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥ መንገዴንም ሁሉ ተቆጣጥረሃል፥ የእግሬንም ዱካ ወስነሃል።

28 እኔ እንደሚበሰብስ የተበላሸ ነገር፥ ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos