ኤርምያስ 35 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሬካባውያን መመስገናቸው 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ 2 “ወደ ሬካባውያን ቤት ሂድና አነጋግራቸው፥ ወደ ጌታም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዱ አስገባቸው የወይን ጠጅም እንዲጠጡ ስጣቸው።” 3 የከባስን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን፥ ወንድሞቹንም፥ ልጆቹንም ሁሉ፥ የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኩ፤ 4 ወደ ጌታም ቤት የደጁ ጠባቂ በሆነው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው በአለቆች ጓዳ አጠገብ ወደሚገኘው፥ ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ አስገባኋቸው። 5 ከዚያም በሬካባውያን ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አስቀምጬ፦ “የወይኑን ጠጅ ጠጡ” አልኳቸው። 6 እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና፦ ‘እናንተና ልጆቻችሁ ለዘለዓለም የወይን ጠጅ አትጠጡ፤ 7 በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንን አትትከሉ ወይም የወይን ቦታ አይኑራችሁ።’ 8 እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ሰምተን፥ ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም ሚስቶቻችንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፤ 9 የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም፤ 10 ሆኖም ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጠናል፥ እኛም በመታዘዝ አባታችን ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል። 11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ፦ ‘የከለዳውያንን ሠራዊትና የሶርያውያንን ሠራዊት በመፍራት ኑ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ’ አልን፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።” 12 የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ቃሎቼን ለመስማት ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል ጌታ። 14 የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹን የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃላት ተፈጸሙ፤ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ አይጠጡም፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ተናገርኋቸው፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም ግን አልሰማችሁኝም። 15 እንዲሁም፦ ‘እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ሥራችሁንም አሳምሩ፥ ልታገለግሉአቸውም ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ’ እያልሁ በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ላክሁባችሁ፤ ላክሁ፥ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም እኔንም አልሰማችሁኝም። 16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል፥ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝም። 17 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሆነ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና በእነርሱ ላይ የተናገርኩትን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በተቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።” 18 ኤርምያስም ለሬካባውያን ቤት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፥ ትእዛዛቱንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም በሙሉ ፈጽማችኋልና፤ 19 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘለዓለም ፈጽሞ አይታጣም።” |