Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 38 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 በዚያም ጊዜ ሕዝቅያስ ለሞት በሚያደርስ ህመም ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው።

2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ ጌታ ጸለየ፦

3 “ጌታ ሆይ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ።” ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።

4 ከዚያም የጌታም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፦

5 “ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ የአባትህ የዳዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ።

6 አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ።

7 “ጌታም የተናገረውን ነገር እንደሚፈጽመው ከጌታ ይህ ምልክት ይሆንልሃል።

8 እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት መቁጠሪያ ላይ በደረጃዎች ያለውን ከፀሐይ ጋር የወረደውን ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላው የሰዓት ስፍራ ላይ በወረደበት ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።

9 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ከበሽታው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሑፍ ይህ ነው፦

10 እኔ፦ በሕይወት ዘመኔ እኩሌታ ከሕይወት ልለይ ይገባልን? በቀረው ዘመኔስ ወደ ሲኦል በሮች መግባት አለብኝን? አልኩ።

11 ደግሞም፦ በሕያዋን ምድር ጌታን አላይም፤ በዓለምም የሚኖሩትን ሰዎች ከእንግዲህ አልመለከትም አልኩ።

12 ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልኩት፤ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ፍጻሜዬን አቀረብከው።

13 እስኪ ነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ፍጻሜዬን አቀረብከው።

14 እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጉረመረምሁ፤ ዐይኖቼ ወደ ላይ በማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ።

15 ግን ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ።

16 “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስከኝ ወደ ሕይወትም መለስከኝ።

17 እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ምክንያት ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጉድጓድ አዳንካት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ።

18 ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጉድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም።

19 እኔ ዛሬ እንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆቹ እውነትህን ያስታውቃል።

20 ጌታ ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።”

21 ኢሳይያስም፦ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፥ እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር።

22 ሕዝቅያስም፦ “ወደ ጌታ ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድነው?” ብሎ ነበር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos