Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 35 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሃውም ሐሤት ያደርጋል፥ እንደ ጽጌረዳም ይፈካል።

2 እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የጌታንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።

3 የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ።

4 ፈሪ ልብ ላላቸው፦ “እነሆ፥ አምላካችሁ ለበቀል፥ ብድራት ለመመለስ ይመጣል፤ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ!” በሉአቸው።

5 በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዐይን ይበራል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል።

6 በዚያን ጊዜ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ምንጭ ይፈልቃልና አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳም ምላስ ይዘምራል።

7 ደረቂቱ ምድር ኩሬ፥ የተጠማች መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ለምለም፥ ሸምበቆው ደንገል ይበቅልበታል።

8 በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፥ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐን ያልሆኑ አያልፉበትም፥ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ግን ያልፉበታል፤ ተጓዦች ሆኑ፥ ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም።

9 አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ እነዚህ ከዚያ አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤

10 ጌታም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፥ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላላም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos