Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 26 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 በዚያም ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፦ የጸናች ከተማ አለችን፤ ቅጥሯንና ምሽጓን ለደኅንነታችን አኑሮታል።

2 በእምነቱ የጸና ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ።

3 በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ በአንተ ላይ ታምናለችና በሰላም ትጠብቃታለህ።

4 ጌታ እግዚአብሔር የዘለዓለም ዐለት ነውና ለዘለዓለም በጌታ ታመኑ።

5 በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያወርዳታል፥ እስከ ትቢያም ድረስ ይጥላታል።

6 እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም ኮቴ፥ ትረግጣታለች።

7 የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንክ የጻድቃንን መንገድ ታቀናለህ።

8 አቤቱ ጌታ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው።

9 ፍርድህን በምድር ላይ በፈረድክ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች።

10 ክፉዎች እድል ቢሰጣቸው እንኳን ጽድቅን አይማሩም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋሉ፥ የጌታንም ግርማ አያዩም።

11 አቤቱ ጌታ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች።

12 አቤቱ ጌታ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ።

13 አቤቱ አምላካችን ጌታ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤ ነገር ግን የአንተን ስም ብቻ እናስባለን።

14 እነርሱ ሞተዋል፥ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፥ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጎብኝተሃቸዋል፤ አጥፍተሃቸውማል፤ መታሰቢያቸውንም ሁሉ እንዳልነበር አድርገሃል።

15 ሕዝብን አበዛህ፥ አቤቱ ጌታ፥ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፥ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ።

16 አቤቱ ጌታ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሠጽሐቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ።

17 የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ አንደምትጮኽ፥ አቤቱ ጌታ፥ በፊትህ እንዲሁ ሆነናል።

18 እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፤ በምድርም ደኅንነት አላመጣንም፤ በዓለም እንዲኖሩም ሕዝብ አልወለድንም።

19 ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።

20 ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን ከጀርባህ ዝጋ፤ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።

21 በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ሊያመጣባቸው፥ እነሆ፥ ጌታ ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ያፈሰሰችውን ደም ትገልጣለች፥ የተገደሉትንም ከእንግዲህ ወዲህ አትሸሽግም።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos