ኢሳይያስ 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጢሮስና ሲዶና 1 ስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት። እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ወደባቹህ ፈርሷልና አልቅሱ፤ ዜናው ከኪትም ምድር ደርሷችኋል። 2 እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፥ በባሕርም የሚሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች የሞሉባችሁ፥ ጸጥ በሉ። 3 በጥልቅ ውኆቿ ላይ የሺሖር እህልና የዓባይ ወንዝ መከር ገቢዋ ነበር፤ እርሷም የአሕዛብ የንግድ መናኸሪያ ነበረች። 4 ባሕሩ “አላማጥሁም፤ አልወለድሁም፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን አላሳደግሁም” ብሏልና፥ አንቺ ሲዶና ሆይ፥ አንቺ የባሕር ምሽግ ሆይ፥ እፈሪ። 5 ከጢሮስ የሚመጣው ዜና፤ በግብጽ በሚሰማበት ጊዜ ጭንቅ ይይዛቸዋል። 6 ወደ ተርሴስም ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ። 7 በጥንት ዘመን ተቆርቁራ የነበረችው፥ እሩቅ ምድር ድረስ እድትሰፍር እግሮችዋ ያጓጓዟት፥ የደስታችሁ ከተማ ይህች ናት? 8 አክሊል በተቀዳጀች፥ ነጋዴዎችዋ መሳፍንት በሆኑ፥ በምድር የከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት፥ በጢሮስ ላይ ይህን ያሰበ ማን ነበር? 9 የክብርን ሁሉ ትዕቢት ሊሽር፥ የምድርንም ክብር ሁሉ ሊያስንቅ የሠራዊት ጌታ ይህን ወስኗል። 10 የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በምድርሽ ላይ ፍሰሺ። 11 እጁን በባሕር ላይ ዘረግቶ መንግሥታትንም አናውጧል፤ የከነዓንም ምሽጎች እንዲፈርሱ ጌታ አዟል። 12 አንቺ የተሰባበርሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ። 13 እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት። 14 እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ። 15 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። 16 አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ። 17 ከሰባ ዓመትም በኋላ ጌታ ጢሮስን ይጎበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትመለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች። 18 ንግድዋና ዋጋው ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋንም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በጌታ ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም። |