ኢሳይያስ 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥ 2 በዚያ ጊዜ ጌታ የዓሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፥ “ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውርድ፤ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ” ብሎ ተናገረው። እንደተባለውም አደረገ፤ ራቁቱን ሆኖ በባዶ እግሩም ሄደ። 3 ጌታም እንዲህ አለ፦ “አገልጋዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት እንዲሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥ 4 እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጉስቁልና ይነዳቸዋል። 5 እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ፤ ያፍራሉም። 6 በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ፥ ‘እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን?’ ይላሉ።” |