ኢሳይያስ 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ በምድር ላይ ገዢ ለሆነው ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ የበግ ጠቦቶችን ስደዱ። 2 ከጎጆቸው ተበትነው እንደሚበሩ ወፎች፥ የሞዓብ ሴቶችም በአርኖን መሻገሪያዎች እንዲሁ ይሆናሉ። 3 ምክርን ለግሺ፥ ፍትህን አስፍኚ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አጢይ፤ ስደተኞችን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አሳልፈሽ አትስጪ። 4 ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ዘንድ ይኑሩ፤ ስደተኞቹን ከሚሳድዷቸው መሸሸጊ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቷል፤ ጨቋኞች የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። 5 ዙፋኑም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም በዳዊት ድንኳን ፍትህን የሚሻ ትክክል የሆነውን ለመፈጸም የሚፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል። 6 የሞዓብን ኩራት፥ እጅግ መታበዩን! ስለ እብሪቱና ስለ ኩራቱ፥ ስለ ስድነቱም ሰምተናል፤ ትምክሕቱ ከንቱ ነው። 7 ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማ፤ ሁሉም ዋይታ ያሰማሉ፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። 8 የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች ኢያዜርን አልፈው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቁጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። 9 ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ግንድ ከኢያዜር ልቅሶ ጋር አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አርስሻለሁ። 10 ደስታና ሐሴትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፤ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። 11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ በገና የኀዘን እንጉርጉሮ ታሰማለች። 12 ሞዓም ወደ ኮረብታ ወጥቶ ራሱን ቢያደክም፥ ለጸሎት ወደ መቅደሱ ቢገባም በከንቱ ይደክማል እንጂ አያሸንፍም። 13 ጌታ በሞዓብ ላይ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ይህ ነው። 14 አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ተቀጣሪ ደሞዝተኛ የሞዓብ ክብር፥ ምንም ያህል ሕዝቡ ቢበዛ፥ በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚተርፈውም ሕዝብ እጅግ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።” |