ኢሳይያስ 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ስለ ሞዓብ የተነገረ ትንቢት 1 የሞዓብ ኤር በሌሊት ፈርሶ ጠፋ፤ ቂር የሚባልም የሞዓብ ምሽግ በሌሊት ፈርሶ ጠፋ። 2 ወደ ባይት ወደ ዲቦንም ወደ ኮረብታ መስገጃዎችም ለልቅሶ ወጥተዋል፤ ሞዓብ በናባውና በሜድባ ላይ ታለቅሳለች፤ ራሳቸው ሁሉ ተነጭቶአል፥ ጢማቸውም ሁሉ ተላጭቷል። 3 በየመንገዳቸውም በማቅ ታጥቀዋል፤ በየሰገነቶቻቸውና በየአደባባዮቻቸው እንባ እጅግ እያፈሰሱ ሁሉም አልቅሰዋል። 4 ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮሁ፥ ድምፃቸው እስከ ያሀፅ ድረስ ተሰማ፤ ስለዚህ የሞዓብ ሰልፈኞች ጮኹ፤ ነፍሱም ራደች። 5 ልቤ ስለ ሞዓብ አለቀሰ፤ ከእርሷ የሚሸሹ ወደ ዞዐር ወደ ዔግላት ሺሊሺያ ኮበለሉ፤ በሉሒት አቀበት ላይ እያለቀሱ ወጡ፤ በሖሮናይምም መንገድ የዋይታ ጩኽት አሰሙ። 6 የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ፤ ሣሩም ደርቋል፤ ለጋውም ጠውልጓል፤ ልምላሜውም ሁሉ የለም። 7 ስለዚህ የሰበሰቡትን ሀብትና መዝገባቸውን ወደ አኻያ ዛፍ ወንዝ ማዶ ይወስዱታል። 8 ጩኸት በሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ያስተጋባል፤ ዋይታም ወደ ኤግላይምና ወደ ብኤርኢሊም ደረሰ። 9 የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ ገና በዲሞን ላይ ሥቃይን እጨምራለሁ፥ ከሞዓባውያንም በሚያመልጡ፥ ከምድርም በሚቀሩ ላይ አንበሳን እሰዳለሁ። |