Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሆሴዕ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በገላጣም ስፍራ ወንበዴ ቀምቶአልና፤ እስራኤልን በፈወስሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ።

2 እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንደማስታውስ ልብ አላደረጉም፤ አሁንም ሥራዎቻቸው ከብበዋቸዋል፥ እነርሱም በፊቴ አሉ።

3 ንጉሡን በክፋታቸው፥ ሹማምንቱንም በሐሰታቸው ደስ ያሰኛሉ።

4 ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ የተለወሰውን ቡኮ እስኪቦካ ድረስ ጋጋሪ እሳቱን ሳይቆሰቁሰው እንደ ተወው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው።

5 በንጉሣችን ቀን ሹማምንቱ ከወይን ጠጅ ሞቅታ የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከፌዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ።

6 በሴራቸው ልባቸው እንደ ምድጃ ተቃጥላለችና፤ ጋጋሪያቸው ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በነጋም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ነደደ።

7 ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም አጥፍተዋል፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወድቀዋል፤ ከእነርሱም መካከል ወደ እኔ የጮኸ የለም።

8 ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ሆነ።

9 ባዕዳን ጉልበቱን በዘበዙ፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም።

10 የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ወደ አምላካቸው ወደ ጌታ ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም።


በአሕዛብ ላይ መደገፍ ከንቱ መሆኑ

11 ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌለው እንደ ሞኝ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ።

12 በመሄድ ላይ ሳሉ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ በጉባኤያቸው ላይ እንደተላለፈው እገሥጻቸዋለሁ።

13 ከእኔ ሸሽተው ሄደዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ እታደጋቸው ነበር፥ እነርሱ ግን ሐሰትን ተናገሩብኝ።

14 በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዓመፁ።

15 ክንዳቸውን ያስተማርሁና ያጸናሁ እኔ ነበርሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን አሴሩብኝ።

16 ከንቱ ወደ ሆነው ነገር ተመለሱ፤ እንደ ረገበ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከክፉ አንደበታቸው የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos