Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 47 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዮሴፍ የዘመዶቹን መምጣት ለፈርዖን መናገሩ

1 ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ከብቶቻቸውንና ሌላም ያላቸውን ነገር ሁሉ ይዘው ከከነዓን ወደዚህ መጥተዋል፤ አሁንም በጌሴም ምድር ይገኛሉ” አለው።

2 ከወንድሞቹ መካከል መርጦ ያመጣቸውንም አምስቱን ወንድሞቹን ወደ ፈርዖን አቀረባቸው።

3 ፈርዖንም ወንድሞቹን፦ “ሥራችሁ ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን፦ “እኛ አገልጋዮችህ፥ እኝም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን” አሉት።

4 “በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፥ የአገልጋዮችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለም፥ አሁንም አገልጋዮችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን።” አሉት ፈርዖንን።

5 ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፥

6 የግብጽ ምድር በፊትህ ናት፥ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፥ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱ መካከል ችሎታ ያላቸው ሰዎች ካሉ፥ በእኔ እንስሶች ላይ የበላይ ኀላፊዎች አድርገህ ሹማቸው።”

7 ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፥ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው።

8 ፈርዖንም ያዕቆብን፦ “የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው?” አለው።

9 ያዕቆብም ለፈርዖን አለው፦ “የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፥ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፋም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።”

10 ፈርዖንን ባርኮም ያዕቆብ ከፈርዖንም ፊት ወጣ።

11 ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብጽ ምድር በተሻለችው የራምሴ ምድር በይዞታ ሰጣቸው።

12 ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው።


የዮሴፍ የግብርና ደንብ

13 ራብም እጅግ ጸንቶአልና፥ በምድር ሁሉ እህል አልነበረም፥ ከራብም የተነሣ የግብጽ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ።

14 ዮሴፍም የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች የመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር።

15 በግብጽ ምድርና በከነዓን ምድር ብሩም በሸመታ አለቀ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉም ወደ ዮሴፍ እየመጡ፦ “የምንመገበው ስጠን፥ ስለምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና” አሉት።

16 ዮሴፍም፦ “ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፥ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ።

17 ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፥ ያንንም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ልዋጭ ህልን መገባቸው።

18 ዓመቱም ተፈጸመ፥ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ከጌታችን አንሰውርም፥ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፥ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፥

19 እኛ በፈትህ ስለምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባርያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፥ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።”

20 ዮሴፍም የግብጽን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፥ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች።

21 ሕዝቡንም ሁሉ ከግብጽ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባርያዎች አደረጋቸው።

22 የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፥ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም።

23 ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፥ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፥

24 በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፥ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ምግብ ይሁን።”

25 እነርሱም፦ “አንተ ሕይወታችንን አተረፍክ፥ ጌታችንን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፥ ለፈርዖንም ባርያዎች እንሆናለን” አሉት።

26 ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዓን እንዲሆን በግብጽ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት።


ያዕቆብ የመጨረሻ ልመና

27 እስራኤልም በግብጽ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፥ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ።

28 ያዕቆብም በግብጽ ምድር ዐሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፥ የያዕቆብም የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው።

29 የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፥ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብጽ ምድርም እንዳትቀብረኝ በታማኝነትና እውነት ቃል ግባልኝ፥

30 ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብጽ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ።” እርሱም፦ “እንደ ቃልህ አደርጋሁ” አለ።

31 እርሱም፦ “ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፥ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos