ዘፍጥረት 32 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም አጋጠሙት። 2 ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ፥ “እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው!” አለ። የዚያንም ስፍራ ስም ማሃናይም ብሎ ጠራው። ከዔሳው ጋር ለመገናኘት የያዕቆብ ዝግጅት 3 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፥ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “ለጌታዬ ለዔሳው፥ አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፥ ‘በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፥ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፥’” ብላችሁ ንገሩት 5 “በሬዎች፥ አህዮች፥ በጎች፥ ወንድ አገልጋዮች፥ እና ሴት አገልጋዮችም አገኘሁ፥ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማሳወቅ ላኩብህ።” 6 መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት፥ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፥ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች” አሉ። 7 ያዕቆብም እጅግ ፈራ ተጨነቀም፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች፥ መንጎችን እና ከብቶችን ግመሎችንም፥ በሁለት ወገን ከፈላቸው፥ 8 “ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።” ብሎም አሰበ። 9 ያዕቆብም አለ፦ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ ጌታ ሆይ፥ 10 ለባርያህ ካሳየኸው ከጽኑ ፍቅርና ከታማኝነትህ ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፥ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበር፥ አሁን ግን ለሁለት ወገን የተከፈልኩ ሆንሁ። 11 ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፥ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። 12 አንተም፦ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ’ ብለህ ነበር።” 13 በዚያችም ሌሊት ከዚያው ሰፈረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን አወጣ፥ 14 ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥ 15 ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ ዐሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ ዐሥርም እህዮችን፤ 16 እነዚህንም መንጎቹ በየወገኑ ከፍሎ በአገልጋዮቹ እጅ አደረጋቸው፥ አገልጋዮቹንም፦ “ከእኔ ቀድማችሁ ሂዱ፥ በመንጋው እና መንጋው መካከልም እርቀት አኑሩ” አለ። 17 የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ “ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ፥ ‘አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው?’ ብሎ የጠየቀህም እንደሆነ፥ 18 በዚያን ጊዜ አንተ፦ ‘ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የላከው የባርያህ የያዕቆብ ነው፥ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው’ በለው።” 19 እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዱሁ ብሎ አዘዘ፦ “ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት። 20 ‘እንዲሁም ባርያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው’ እንድትሉት። እሱ ‘በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይቀበለኛል ፊቱንም አያለሁ’ ብሎ አስቧል።” 21 ስለዚህ እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፥ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት እዚያው በሰፈሩበት አደረ። የያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር መታገል 22 በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹን፥ እና ዐሥራ አንዱን ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። 23 እነርሱን ወስዶ ወንዙን አሻገራቸው፥ ያለውን ሁሉ እንደዚሁ አሻገረ። 24 ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፥ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ሲታገለው አደረ። 25 ያ ሰው ያዕቆብን እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ፥ የጭኑን ሹልዳ ነካው፥ ያዕቆብም ሲታገለው የጭኑ ሹልዳ ከመገጣጠሚያው ላይ ተለያየ፤። 26 ከዚያ ሰውየው፦ “የንጋት ጎህ ሊቀድ ነውና ልቀቀኝ” አለው። እርሱም፦ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። 27 ሰውየውም፦ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፦ “ያዕቆብ ነኝ” አለው። 28 ሰውየውም፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ ያዕቆብ አይባልም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና እስራኤል ይባላል” አለው። 29 ያዕቆብም፦ “ልለምንህ፥ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ “ስሜን ለምን ትጠይቃለህ?” አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው። 30 ስለዚህ ያዕቆብ፦ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሆኖም ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል የዚያን ቦታ ስም “ጵኒኤል” ብሎ ጠራው። 31 ጵኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32 ስለዚህም የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርቹን ሹልዳ ነክቶታልና፥ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን (በጭን መጋጠሚያ ላይ ያለውን) ሹልዳ አይበሉም። |