ዕዝራ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የዕዝራ መምጣትና የሠራው ሥራ 1 ከነዚህም ነገሮች በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥ የዓዛርያ ልጅ፥ የሒልቂያ ልጅ፥ 2 የሻሉም ልጅ፥ የጻዶቅ ልጅ፥ የአሒጡብ ልጅ፥ 3 የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥ 4 የዘራሕያ ልጅ፥ የዑዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ 5 የአቢሹዓ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የኤልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ 6 ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ችሎታ ያለው ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩ የጌታ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው። 7 በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ፥ ከካህናቱም አንዳንዶቹ፥ ሌዋውያኑ፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹና፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 8 በንጉሡ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛውም ወር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 9 በመጀመሪያው ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን መውጣት ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። 10 ዕዝራም የጌታን ሕግ ሊፈልግና ሊያደርግው፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ሊያስተምር ልቡን አዘጋጅቶ ነበር። አርጤክስስ ለዕዝራ የሰጠው ደብዳቤ 11 የጌታን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ ንጉሡ አርጤክስስ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው፦ 12 “ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ ለሰማያት አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ዕዝራ፤ አሁንም 13 በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ፥ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ የሚፈልግ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ። 14 በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል፤ 15 ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤ 16 በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚሰጡትን ይዘህ ሂድ። 17 ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወይፈኖችን፥ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን ከእህል ቁርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቁርባኖቻቸው ጋር ተግተህ ግዛ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው። 18 የሚቀረውን ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ለማድረግ ደስ የሚላችሁን ነገር አድርጉ። 19 ለአምላክህ ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃዎች በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ። 20 ከዚህ በላይ ለአምላክህ ቤት የሚያስፈልግህን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ቤተ መዛግብት ውሰድ። 21 እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ለምትገኙ ገንዘብ ያዦች ሁሉ፦ የሰማያት አምላክ ሕግ ጸሐፊ የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ 22 እስከ መቶ መክሊት ብር፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶ የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት፥ ጨውም የሚፈልገውን ያህል ሳትጽፉ ስጡት። 23 በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቁጣ እንዳይሆን፥ የሰማያት አምላክ የሚያዘው ሁሉ ልክ እንዳዘዘው ለሰማያት አምላክ ቤት ይደረግ። 24 ደግሞም በካህናቱ፥ በሌዋውያኑ፥ በመዘምራኑ፥ በበር ጠባቂዎቹና፥ በቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም ለመጣል ሥልጣን እንደሌላችሁ እወቁ። 25 አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ለሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ እንዲፈርዱ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፥ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው። 26 የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ትእዛዝ በማያደርግ በማንም ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ንብረት መወረስ ወይም ግዞት በፅኑ ይፈረድበት።” 27 በኢየሩሳሌም ያለውን የጌታን ቤት እንዲያሳምር እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ የአባቶቻችን አምላክ ጌታ ይባረክ። 28 በንጉሡ፥ በአማካሪዎቹና በኃያላን ባለሥልጣኖቹም ሁሉ ፊት ፅኑ ፍቅሩን በእኔ ላይ ዘረጋ፤ እኔም በላዬ ባለችው በእግዚአብሔር እጅ ራሴን አበረታሁ፥ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል አለቆችን ሰበሰብሁ። |