Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሕዝቅኤል 43 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


መለኮታዊው ክብር ወደ መቅደሱ መመለሱ

1 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በር አመጣኝ።

2 እነሆ፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከወደ ምሥራቅ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ድምጽ ነበር፥ ከክብሩ የተነሣ ምድር ታበራ ነበር።

3 ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።

4 የጌታ ክብር በሩ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው ቤት ገባ።

5 መንፈስም አነሣኝ፥ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አስገባኝ፤ እነሆ፥ የጌታ ክብር ቤቱን ሞላው።

6 ከቤቱ ውስጥ ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፥ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር።

7 እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘለዓለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ ማሳረፊያ ይህ ነው። የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በዝሙታቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ዳግመኛ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።

8 መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውን በመቃኔ አጠገብ በማድረጋቸው፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ግንብ ብቻ ቀረ፥ በሠሩት ርኩሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፥ ስለዚህ በቁጣዬ አጠፋኋቸው።

9 አሁንም ዝሙታቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፥ እኔም ለዘለዓለም በመካከላቸው እኖራለሁ።

10 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ በኃጢአታቸው እንዲያፍሩ ለእስራኤል ቤት ስለ ቤቱ ንገራቸው፥ ንድፉንም ይለኩ።

11 በሠሩት ሥራ ሁሉ የሚያፍሩ ከሆነ፥ የቤቱን ንድፉንና አሠራሩን፥ መውጫውንና መግቢያውን፥ አጠቃላይ ንድፉን፥ ሥርዓቱን ሁሉ፥ ንድፉን ሁሉ፥ ሕጉን ሁሉ አሳውቃቸው፤ ንድፉን ሁሉና ሥርዓቱን ሁሉ እንዲያዩትና እንዲያደርጉትም በፊታቸው ጻፈው።

12 የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ በዙሪያው ያለው ስፍራ ሁሉ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።


ስለ መሠዊያው

13 የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፤ ክንዱም አንድ ክንድ ከስንዝር ነው። መሠረቱ ቁመቱ አንድ ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ ዙሪያውም አንድ ስንዝር ጠርዝ አለው፤ ይህም የመሠዊያው ከፍታ ነው።

14 መሬት ላይ ካለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹ እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው።

15 የመሠዊያው ምድጃው አራት ክንድ ነው፤ ከመሠዊያው ምድጃ በላይ አራት ቀንዶች አሉ።

16 የመሠዊያው ምድጃ ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን እኩል ነው።

17 የእርከኑም ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ ወርዱም ዐሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን እኩል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ጠርዝ ግማሽ ክንድ ነው፥ የመሠረቱም ዙሪያ አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹ ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።

18 እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መሠዊያው ተሰርቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በላዩ በሚያቀርቡበት ደምንም በላዩ በሚረጩበት ቀን የመሠዊያው ሥርዓት ይህ ነው።

19 ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ለካህናት፥ ከሳዶቅ ዘር ለሆኑ ለሌዋውያን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

20 ከደሙ ትወስዳለህ፥ በአራቱ ቀንዶቹ፥ በእርከኑ፥ በአራቱ ማዕዘን ላይ፥ በዙሪያውም ባለው ጠርዝ ላይ ታደርጋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ ታጠራዋለህም።

21 ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፥ ከመቅደሱ ውጭ ባለው ቤት በተወሰነው ስፍራ ይቃጠላል።

22 በሁለተኛውም ቀን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል።

23 ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈንና ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ ታቀርባለህ።

24 በጌታ ፊት ታቀርባቸዋለህ፥ ካህናቱም በላያቸው ላይ ጨው ይነስንሱባቸው፥ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡአቸዋል።

25 ሰባት ቀን በየዕለቱ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየልን ታቀርባለህ፥ ነውር የሌለባቸውን ከመንጋው አንድ ወይፈን ከመንጋው አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ።

26 ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርያሉ ያነጹታልም፥ እጃቸውን ይሞላሉ።

27 ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀንና ከዚያም በኋላ፥ ካህናቱ የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና የሰላም መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos