Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሕዝቅኤል 40 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአዲሱ ቤተ መቅደስ ራእይ

1 በተሰደድን በሀያ አምስተኛው ዓመት፥ በዓመቱ መጀመሪያ፥ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ በተመታች በዓሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረ፥ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።

2 በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፥ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም በደቡብ በኩል ከተማ የሚመስል ሕንፃ ነበረ።

3 ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆ፥ መልኩ ናስ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ይዞ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር።

4 ሰውዬውም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓይንህ እይ፥ በጆሮህም ስማ፥ የማሳይህን ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል፥ ይህን እንዳሳይህ ወደዚህ ተመርተሃልና የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር።”

5 እነሆ፥ በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ ያለው የመለኪያው ዘንግ ርዝመት አንድ ክንድ ከስንዝር የሆነ ስድስት ክንድ ነበረ፤ ቅጥሩንም ለካ፥ ስፋቱ አንድ ዘንግ፥ ቁመቱም አንድ ዘንግ ነበር።

6 ፊቱ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በር መጣ፥ በደረጃዎቹም ወጥቶ በበሩ በኩል ያለውን የቤቱን መግቢያ ወለል ወርዱን ለካ አንድ ዘንግ ነበር፥ የሌላኛውም የቤቱ መግቢያ ወለል ወርድ አንድ ዘንግ ነበር።

7 ክፍሉም ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በክፍሎቹ መካከል ያለው ርቀት አምስት ክንድ ነበረ፤ ከበራፉም በውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ መተላለፊያ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ።

8 በውስጥ ያለውን የበሩን መተላለፊያ ለካ አንድ ዘንግ ነበር።

9 የበሩን መተላለፊያ ስምንት ክንድ፥ የግንቡንም አዕማድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም መተላለፊያ በውስጥ በኩል ነበረ።

10 የምሥራቁ በር ጓዳዎች በዚህ በኩል ሦስት በዚያ በኩል ደግሞ ሦስት ነበሩ፥ ሦስቱም እኩል ስፋት ነበራቸው፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል እኩል ነበረ።

11 የበሩን መግቢያ ወርድ ዐሥር ክንድ፥ የበሩን ርዝመት ዐሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ።

12 በጓዳዎቹም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ ጓዳውም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበረ።

13 ከአንዱ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩ ወርድ ሀያ አምስት ክንድ ሆነ፤ መዝጊያውና መዝጊያውም ትይዩ ነበረ።

14 መተላለፊያውን ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም መተላለፊያ ዙሪያ አደባባይ ነበረ።

15 ከበሩ መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ መተላለፊያ መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ።

16 ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ ትናንሽ መስኮቶች ነበሩአቸው፤ ደግሞም በመተላለፊያው ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።

17 ከዚያም ወደ ውጪው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆ በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ።

18 በበሮቹ አጠገብ የነበረው ወለል ርዝመት እንደ በሮቹ መጠን ነበረ፤ ይህም ታችኛው ወለል ነበረ።

19 ከታችኛው በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

20 በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከተውን በር ርዝመትና ወርዱን ለካ።

21 ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ እንደ ፊተኛው በር መጠናቸው እኩል ነበር፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበር።

22 መስኮቶቹ፥ መተላለፊያዎቹና የዘንባባ ዛፎቹ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር ካሉት ጋር መጠናቸው እኩል ነበር። ወደ እርሱ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያዎቹም በፊት ለፊቱ ነበሩ።

23 በምሥራቁ በር እንዳለው ዓይነት በሰሜኑ በር ትይዩ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባ በር ነበር፤ ከአንዱ በር እስከ ሌላው በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

24 ወደ ደቡብ መራኝ፥ እነሆ ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መተላለፊያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ። ከሌሎቹም ጋር እኩል መጠን ነበራቸው።

25 በእርሱና በመተላለፊያዎቹም ዙሪያ ሌሎቹን መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩት፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።

26 ወደ እርሱ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መተላለፊያዎቹም በፊት ለፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።

27 በውስጠኛው አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ በደቡብ በኩልም ከበር እስከ በር ድረስ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

28 በደቡብ በር በኩል ወዳለው ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የደቡብንም በር ለካ፤ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበረው።

29 ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።

30 በዙሪያውም መተላለፊያዎች ነበሩ፤ ርዝመታቸው ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸው ደግሞ አምስት ክንድ ነበረ።

31 መተላለፊያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

32 በምሥራቅ በኩል ወዳለው ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤

33 ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።

34 መተላለፊያዎቹም ወደ ውጪው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

35 በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ እርሱንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤

36 ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።

37 የግንቡ አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡ አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

38 በበሮቹ መተላለፊያ አጠገብ በር ያለው ዕቃ ቤት ነበረ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር።

39 የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የበደሉን መሥዋዕት እንዲያርዱባቸው፥ በበሩ መተላለፊያ በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ።

40 ከመተላለፊያው በስተ ውጭ በሰሜን በኩል ባለው በር መግቢያ አጠገብ፥ ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በበሩ መተላለፊያ በሌላኛው ወገን በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ።

41 በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ።

42 ለሚቃጠለው መሥዋዕት ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ወርዳቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመታቸው ደግሞ አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት የሚያርዱበትን ዕቃዎች የሚያስቀምጡባቸው፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ።

43 በቤቱም ዙሪያ አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ ተደርጎላቸው ነበር፤ በገበታዎቹም ላይ የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቀመጥባቸው ነበር።

44 በውስጠኛው መግቢያ በውጭው በኩል በውስጠኛው አደባባይ ለሚዘምሩ ዕቃ ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከት በር አጠገብ ነበረ፥ ወደ ደቡብም ይመለከት ነበር፤ ሌላው ደግሞ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፥ ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር።

45 እንዲህም አለኝ፦ “ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ቤቱን ለሚጠብቁ ካህናት ነው፥

46 ወደ ሰሜን የሚመለከተው ቤት መሠዊያውን ለሚጠብቁ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል እንዲያገለግሉት ወደ ጌታ የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው።”

47 አደባባዩንም ለካ፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ወርዱም መቶ ክንድ አራት ማዕዘን ነበር፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ።


ቤተ መቅደሱ

48 ወደ ቤቱም መተላለፊያ አገባኝ፥ የመተላለፊያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበረ፤ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ።

49 የመተላለፊያው ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ወርዱ ደግሞ ዐሥራ አንድ ክንድ ነበረ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን አንድ በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos