ሕዝቅኤል 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የኢየሩሳሌም መከበብ በስዕል እንደ ተገለፀ 1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለራስህ ጡብን ውሰድ፥ በፊትህም አኑራት፥ በላይዋ ላይም የኢየሩሳሌምን ሥዕል ሳልባት፤ 2 ክበባት፥ ምሽግም ሥራባት፥ ቁልልም ሥራባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም ቅጥርን የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት። 3 የብረት ምጣድም ውሰድ፥ በአንተና በከተማይቱ መካከል የብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርሷ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች፥ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል። 4 አንተም በግራ ጐንህ ተኛ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፥ በምትተኛበትም ቀኖች ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ። 5 እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀኖች ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ። 6 እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ ድጋሚ በቀኝ ጐንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፥ አንድን ዓመት እንደ አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ። 7 ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ፊትህን ታዞራለህ፥ ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ትንቢትን ትናገርባታለህ። 8 እነሆም ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ቀኖች እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጎንህ ወደ ሌላው ጎንህ አትገላበጥም። 9 አንተም ለራስህ ስንዴና ገብስ፥ ባቄላና ምስር፥ ማሽላና አጃን ውሰድ፥ በአንድ ዕቃ ውስጥ አድርጋቸው፥ ለራስህም ምግብ አዘጋጅ፥ በጎንህ እንደ ምትተኛበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ። 10 የምትመገበውም ምግብ በሚዛን በየቀኑ ሃያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜውም ትበላለህ። 11 ውኃም በልክ ትጠጣለህ፥ የኢን መስፈሪያ አንድ ስድስተኛ ትጠጣለህ፥ በየጊዜውም ትጠጣለህ። 12 እንደ ገብስ እንጐቻ አድርገህም ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለህ። 13 ጌታም እንዲህ አለ፦ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ርኩስ ምግባቸውን በምበትንባቸው አገሮች መካከል ይበላሉ። 14 እኔም እንዲህ አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወይኔ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፥ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ፥ የሞተ ወይም እንስሳ የገደለውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም። 15 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ተመልከት በሰው ፋንድያ ፈንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ፥ ምግብህንም በእርሱ አዘጋጅ። 16 ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ እኔ በኢየሩሳሌም የምግብን በትር እሰብራለሁ፥ ምግብ እየፈሩ በሚዛን ይበላሉ፥ ውኃም እየደነገጡ በልክ ይጠጣሉ፤ 17 ይህም ምግብና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲመነምኑ ነው። |