Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 እርሱም እንንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የቀረበልኽን ብላ፥ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር።

2 አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ።

3 እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።

4 እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ንገራቸው።

5 ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ ሕዝብ አልተላክህምና፥

6 ንግግራቸው ጥልቅ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ፥ ቃላቸውንም መስማት ወደማይቻልህ ታላላቅ ሕዝቦች አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ ይሰሙህ ነበር።

7 ነገር ግን የእስራኤል ቤት እኔን መስማት እንቢ ብለዋልና አንተንም አይሰሙህም፥ ምክንያቱም የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና።

8 እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ።

9 ግምባርህን ከባልጩት እንደሚጠነክር አልማዝ አድርጌዋለሁ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አትፍራቸው፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ።

10 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ያዝ፥ በጆሮህም ስማ።

11 ተነሥተህም ወደ ተማረኩት፥ ወደ ሕዝብህ ልጆች ሂድ፥ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው።


ሕዝቅኤል በኮቦር ወንዝ

12 መንፈስም አነሣኝ፥ ከኋላዬም የጌታ ክብር ከሥፍራው ይባረክ የሚል ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ሰማሁ።

13 ይህም የሕያዋኑ ክንፎች እርስ በእርሳቸው ሲማቱ የሚወጣው ድምፅ፥ በአጠገባቸውም የነበሩት የመንኰራኵሮች ድምፅ ነበር፥ እርሱም ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ነበር።

14 መንፈስ አነሳኝ፥ ወሰደኝም፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቁጣ ሄድሁ፥ የጌታም እጅ በላዬ ላይ በርትታ ነበር።

15 በኮቦር ወንዝ አጠገብ ወደሚኖሩ፥ በቴልአቢብም ወዳሉ ምርኮኞች መጣሁ፥ በዚያ በሚኖሩበትም ሰባት ቀን በመካከላቸው በድንጋጤ ተቀመጥሁ።

16 ከሰባቱም ቀን በኋላ የጌታ ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እንዲህም አለኝ፦

17 የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፥ የአፌን ቃል በሰማህ ጊዜ ታስጠነቅቅልኛለህ።

18 እኔ ኃጢአተኛውን፦ ሞትን ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ ካላስጠነቀቅኸው፥ ከክፉ መንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን አስጠንቅቀህ ካልነገርኸው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።

19 ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው፥ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ እርሱ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።

20 ጻድቁ ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት ከሠራ፥ እኔም በፊቱ ዕንቅፋትን አደርጋለሁ፥ እርሱም ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል፥ የጽድቁም ሥራ አይታሰብለትም፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።

21 ነገር ግን ጻድቁን ኃጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀው፥ ጻድቁም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፥ አንተም ነፍስህን አድነሃል።


የሕዝቅኤል መገለልና ዝም ማለት

22 በዚያም የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ተነሥ፥ ወደ ሜዳ ውጣ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ።

23 እኔም ተነሥቼ ወደ ሜዳው ወጣሁ፥ እነሆ በዚያ በኮቦር ወንዝ ያየሁትን ክብር የሚመስል የጌታ ክብር ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ።

24 መንፈስም ገባብኝ፥ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ፦ ሂድ፥ በቤትህ ውስጥ ዘግተህ ተቀመጥ።

25 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ ገመድ ያደርጉብሃል፥ ከእነሱም ጋር ያስሩሃል፥ ከመካከላቸውም አትወጣም፤

26 ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ፥ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚገስጽ ሰው አትሆንባቸውም።

27 ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos