Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሕዝቅኤል 26 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በጢሮስ ላይ የተነገረ አዋጅ

1 እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ፦ “እሰይ የሕዝቦች በር የነበረች ተሰበረች፤ ወደ እኔም ተመለሰች፤ እርሷ ስለፈረሰች እኔ እሞላለሁ፤” ብላለችና።

3 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ! እነሆ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፥ ባሕር ሞገድን እንደሚያስነሣ እንዲሁ ብዙ ሕዝቦችን አስነሣብሻለሁ።

4 የጢሮስን ቅጥሮች ያፈርሳሉ፥ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ አፈሯን ከእርሷ ላይ ጠርጌ የተራቆተ ዓለት አደርጋታለሁ።

5 በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ለሕዝቦችም ብዝበዛ ትሆናለች።

6 በሜዳ ያሉት ሴቶች ልጆችዋም በሰይፍ ይገደላሉ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

7 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነዖርን ከፈረሶች፥ ከሰረገሎች፥ ከፈረሰኞች፥ ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ።

8 በሜዳ ያሉትን ሴቶችን ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፤ በአንቺ ላይ ምሽግ ይሠራል፥ ደለልም በአንቺ ላይ ይደለድላል፥ በአንቺም ላይ ጋሻ ያነሣል።

9 ግንብ ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያነጣጥራል፥ ግንብሽንም በሰይፉ ያፈርሳል።

10 ከፈረሶቹ ብዛት የተነሣ አቧራቸው ይሸፍንሻል፤ ሰዎች ወደ ፈረስች ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ፥ ከፈረሰኞች፥ ከመንኩራኩሮች እና ከሰረገሎች ድምፅ የተነሣ ቅጥሮችሽ ይናወጣሉ።

11 በፈረሶቹ ኮቴዎች ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረጋግጣል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽ ምሰሶዎች ወደ መሬት ይወድቃሉ።

12 ሀብትሽን ይዘርፋሉ፥ ሸቀጣ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽን ያፈርሳሉ፥ የተዋቡ ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽን፥ እንጨትሽንና አፈርሽን በውኆች መካከል ያስቀምጣሉ።

13 የዘፈንሽን ብዛት አስቆማለሁ፤ የበገናሽ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም።

14 የተራቆተ ዓለት አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ዳግምም አትሠሪም፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15 ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል፦ የቆሰሉት ባቃሰቱ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች አይነዋወጡምን?

16 በዚያን ጊዜ የባሕር አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያስቀምጣሉ፥ ወርቀዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ይለብሳሉ፥ በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ፥ በአንቺም ይደነቃሉ።

17 በአንቺ ላይ ሙሾ ያወርዳሉ፥ እንዲህም ይሉሻል፦ ከባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ ዝነኛ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ!

18 አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕር ያሉ ደሴቶችም ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ።

19 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ጥልቁንም በላይሽ ላይ ባመጣሁብሽ ጊዜ፥ ብዙ ውኆችም ይከድኑሻል፥

20 የጥንት ሕዝብ ወዳሉበት ጉድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፥ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም።

21 ለድንጋጤ አደርግሻለሁ፥ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘለዓለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos