Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሕዝቅኤል 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የማፍያ ድስት

1 በዘጠነኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዛሬዋ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ።

3 ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣደው፥ ድስቱን ጣደው፥ ውኃም ጨምርበት።

4 የስጋ ቁራጮች፥ መልካም የሆነው የስጋ ቁራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በውስጡ ጨምር፤ የተመረጡ አጥንቶችንም ሙላበት።

5 የተመረጠውን መንጋ ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ ከስሩ ማገዶ ጨምር፤ በደንብ ይንተክተክ፥ አጥንቶቹም በውስጡ ይብሰሉ።

6 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርሷ ላልወጣ ድስት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቁራጭ ቁራጩን አውጣ፥ ዕጣ አልወደቀባትም።

7 ደምዋ በመካከሏ አለና፤ በተራቆተ ድንጋይ ላይ አስቀመጠችው፤ በአፈር እንዲከደን መሬት ላይ አላፈሰሰችውም።

8 እንድቆጣና፥ በቀልንም እንድበቀል፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቆተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ።

9 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶውን ብዙ አደርገዋለሁ።

10 እንጨቶችን ጨምር፥ እሳቱን አንድድ፥ ሥጋውን ቀቅል፥ ማጣፈጫ ጨምረህ አደባልቀው፥ አጥንቶቹ ይቃጠሉ።

11 እንድትሞቅ፥ ናስዋም እንድትግል፥ ርኩሰትዋም በውስጧ እንዲቀልጥ ዝገትዋም እንዲጠፋ ባዶዋን ፍም ላይ አስቀምጣት።

12 ብዙ ለፍታ ደከመች፥ ሆኖም የዝገቱ ክምር በእሳት እንኳ አልለቀቀም።

13 በርኩሰትሽ ሴሰኝነት አለ፥ መዓቴን በአንቺ ላይ እስክጨርስ ድረስ ከእንግዲህ ወዲያ ከርኩሰትሽ ንፁህ አትሆኚም ምክንያቱም አነጻሁሽ ነገር ግን ንፁህ አልሆንሺምና።

14 እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፤ ይፈፀማል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልቆጠብም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም። እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።


የሕዝቅኤል በሚስቱ ሞት ማዘን

15 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

16 የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የዐይንህን ምኞት በቅፅበት እወስድብሃለሁ፤ ቢሆንም ግን ዋይታ አታሰማ፥ አታልቅስ፥ እንባህንም አታፍስስ።

17 በዝምታ ተክዝ፥ ለሙታን አታልቅስ፤ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፤ ከንፈርህን አትሸፍን፥ የዕዝን እንጀራም አትብላ።

18 እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በማግስቱም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19 ሕዝቡም፦ “እነዚህ የምታደርጋቸውው ነገሮች ለእኛ ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ።

20 እኔም እንዲህ አልኋቸው፦ “የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

21 ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የኃይላችሁ ትምክሕት፥ የዓይናችሁ ምኞት፥ የነፍሳችሁ ናፍቆት የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።

22 እኔ እንዳደረግሁ እናንተም ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም፥ የዕዝን እንጀራም አትበሉም።

23 መጠምጠሚያችሁ በራሳችሁ ላይ፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም ወይም አታለቅሱም፤ በኃጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፥ እርስ በእርሳችሁም ታለቅሳላችሁ።

24 እንግዲህ ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ ያደረገውን ሁሉ እናንተም ታደርጋላችሁ። ይህ በሚመጣበት ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”

25 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ምሽጋቸውን፥ የክብራቸውን ደስታ፥ የዓይናቸውን ምኞት፥ የነፍሳቸውን ናፍቆት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥

26 በዚያን ቀን፥ ያመለጠ ሰው ይህን ነገር ጆሮዎችህ እንዲሰሙ ወደ አንተ ይመጣል።

27 በዚያን ቀን አፍህ ላመለጠው ሰው ይከፈታል፥ ትናገራለህም፥ ከዚያ በኋላም ድዳ አትሆንም። ስለዚህ ምልክት ትሆናቸዋለህ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos