ሕዝቅኤል 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የተመዘዘው የእግዚአብሔር ሰይፍ 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አድርግ፥ ስለ መቅደሶችም ስበክ፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተናገር 3 ለእስራኤልም ምድር እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ሰይፌን ከሰገባው እመዝዘዋለሁ፥ ጻድቁንና ክፉውን ከአንቺ ዘንድ አስወግዳለሁ። 4 ጻድቁንና ክፉውን ከአንቺ ዘንድ ስለማስወግድ፥ ስለዚህ ሰይፌ ከደቡብ እስከ ሰሜን ባለ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል። 5 እኔ ጌታ ሰይፌን ከሰገባው እንደ መዘዝሁ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ደግሞ ወደ ሰገባው አይመለስም። 6 አንተም የሰው ልጅ ሆይ አልቅስ፥ ወገብህን በማጉበጥና በምሬት በፊታቸው አልቅስ። 7 እነርሱም ለምን ታለቅሳለህ? ሲሉህ እንዲህ በላቸው፦ ወሬ ስለሚመጣ ነው፥ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፥ እጆች ሁሉ ይዝላሉ፥ ነፍስ ሁሉ ትደክማለች፥ ጉልበት ሁሉ እንደ ውኃ ይፈስሳል፥ እነሆ ይመጣል ይፈጸማልም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 8 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9 የሰው ልጅ ሆይ፦ ትንቢት ተናገር፥ እንዲህም በል፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ! የተሳለና የተወለወለ ሰይፍ ነው። 10 እንዲገድል ተስሎአል እንዲያብረቀርቅም ተወልውሏል፥ እኛስ ደስ ይለናልን? የልጄን በትር እንደ ማንኛውም ዛፍ ንቆታል። 11 ሰይፉ እንዲወለወል፥ በእጅም እንዲያዝ ተሰጠ፤ በገዳዩ እጅ እንዲቀመጥ ተሳለ፥ ተወለወለም። 12 የሰው ልጅ ሆይ፥ ጩኽ ዋይም በል፥ በሕዝቤ ላይ ነውና፤ በእስራኤል አለቆች ሁሉ ላይ ነውና፤ እነርሱ ከሕዝቤ ጋር ወደ ሰይፍ ተጥለዋል፥ ስለዚህ ጭንህን ምታ። 13 ፈተና ተደርጓል፥ ደግሞ የተናቀ በትር ባይኖርስ ምን ይሆናል? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14 አንተም የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር፥ መዳፍህን በመዳፍህ ምታ፥ የተገደሉ ሰዎች ሰይፍ ሦስት ጊዜ ይደጋግም የሚከብባቸው የተገደለ የታላቅ ሰው ሰይፍ ነው። 15 ልብ እንዲቀልጥ፥ ብዙዎች እንዲሰናከሉ ነው፤ በበሮቻቸው ሁሉ ላይ የሚገድል ሰይፍ አድርጌአለሁ፥ ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሎአል፥ እንዲገድልም ተጠቅልሎአል። 16 ተዘጋጅተህ ፊትህ ወደ ወደደው ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሂድ። 17 እኔም ደግሞ መዳፌን በመዳፌ እመታለሁ፥ ቁጣዬም ይበርዳል፥ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ። 18 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 19 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣበትን ሁለት መንገዶችን አድርግ፥ ሁለቱም ከአንዲት ምድር ይውጡ፥ ምልክትም አድርግ፥ በከተማይቱ መንገድ ራስ ላይ አድርገው። 20 ሰይፍ ወደ አሞን ልጆች ወደ ረባት፥ ወደ ይሁዳ፥ ወደ ተመሸገች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ መንገድን አድርግ። 21 የባቢሎን ንጉሥ ምዋርቱን ያምዋርት ዘንድ በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ መንገዶች ራስ ላይ ቆሞ ነበር፤ ፍላጾችን ወዘወዘ፥ ከተራፊምም ጠየቀ፥ ጉበትም ተመለከተ። 22 የቅጥሩን ማፍረሻ ያደርግ ዘንድ፥ አፍንም በጩኸት ይከፍት ዘንድ፥ በውካታም ድምፅን ከፍ ያደርግ ዘንድ፥ የቅጥሩን ማፍረሻ በበሮች ላይ ያደርግ ዘንድ፥ አፈርን ይደለድል ዘንድ፥ ምሽግም ይሠራ ዘንድ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ውስጥ ነበረ። 23 መሐላውንም በማሉ በዓይናቸው ዘንድ የሐሰት ምዋርት ይመስላል፥ ነገር ግን እነርሱ ይያዙ ዘንድ እርሱ ኃጢአትን ያሳስባል። 24 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኃጢአታችሁን ስለ አሰባችሁ መተላለፋችሁም ስለ ተገለጠ ኃጢአታችሁም በሥራችሁ ሁሉ ስለ ታየ እናንተም ስለ ታሰባችሁ፥ በእጅ ትያዛላችሁ። 25 አንተም ቀንህ የደረሰብህ፥ የኃጢአትህ ቀጠሮ ጊዜ የደረሰብህ፥ ርኩስ ኃጢአተኛ የእስራኤል አለቃ ሆይ፥ 26 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መጠምጠሚያውን አውልቅ፥ ዘውዱንም አርቅ፤ ይህ እንዲህ አይሆንም፤ የተዋረደውን ከፍ አድርግ፥ ከፍ ያለውንም አዋርድ። 27 ባድማ፥ ባድማ፥ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ፍርድ ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ አትሆንም፥ ለእርሱም እሰጣለሁ። 28 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፦ ጌታ እግዚአብሔር ስለ አሞን ልጆችና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ቀናቸው በደረሰ፥ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ በደረሰ፥ በተገደሉት ኃጢአተኞች 29 አንገት ላይ ያኖሩህ ዘንድ ከንቱን ራእይ ነገር ሲያዩልህ በሐሰትም ምዋርት ሲናገሩልህ፦ ሰይፍ፥ ሰይፍ ተመዝዞአል፥ ይገድልም ዘንድ ያብረቀርቅም ዘንድ ተሰንግሎአል በል። 30 ወደ ሰገባው መልሰው። በተፈጠርህበት ስፍራ በተወለድህባትም ምድር እፈርድብሃለሁ። 31 ቁጣዬንም አፈስስብሃለሁ፥ በመዓቴም እሳት አነድብሃለሁ፥ ማጥፋትንም ለሚያውቁ ለጨካኞች ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 32 ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፥ ደምህም በምድር መካከል ይሆናል፥ ደግሞም አትታሰብም፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁና። |