ሕዝቅኤል 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የጥቅሉ ራእይ 1 እርሱም፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ ከአንተ ጋር እንድነጋገር በእግርህ ቁም” አለኝ። 2 ሲያናግረኝም መንፈስ ገባብኝ፥ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ። 3 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ወደ እስራኤል ልጆች፥ ወደ ዓመፀኞች አገር፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁት እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ቀን ድረስ በእኔ ላይ ዐመፁ። 4 ፊታቸው የተኮሳተረና ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው፥ እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፥ አንተም እንዲህ በላቸው፦ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤” 5 እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ ያውቃሉ። 6 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ኩርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራ፥ ቃላቸውንም አትፍራ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቃላቸውን አትፍራ፥ ፊታቸውንም አትፍራው። 7 እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙም ባይሰሙም ቃሌን ትነግራቸዋለህ። 8 አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፥ አፍህን ክፈት፥ የምሰጥህንም ብላ። 9 ተመለከትሁም፥ እነሆ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፥ እነሆ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት። 10 በፊቴም ዘረጋው፥ በፊቱና በኋለውም ልቅሶ፥ ኃዘንና ዋይታም ተጽፎበት ነበር። |