ዘፀአት 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)5. የከብቶች ዕልቂት 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል፥ ብትይዛቸውም፥ 3 እነሆ የጌታ እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶች፥ በአህዮች፥ በግመሎች፥ በበሬዎችና በበጎች ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ተላላፊ በሽታ ይወርዳል። 4 ጌታም በእስራኤልና በግብጽ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አይሞትም።’” 5 ጌታም፦ “ነገ ጌታ ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል” ብሎ ጊዜን ወሰነ። 6 ጌታም ያንን ነገር በማግስቱ አደረገ፥ የግብጽም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። 7 ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም። 6. ብጉንጅ 8 ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማያት ይበትነዋል። 9 እርሱም በግብጽ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብጽም ምድር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ፈሳሽ የሚያወጣ ብጉንጅ ይሆናል።” 10 ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማያት በተነው፥ በሰውና በእንስሳ ላይም ፈሳሽ የሚያወጣ ብጉንጅ ሆነ። 11 ብጉንጅ በጠንቋዮቹና በግብጻውያን ሁሉ ላይ ነበር፤ ጠንቋዮቹም ብጉንጅ ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ 12 ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ ጌታ ሙሴን እንደ ተናገረው ፈርዖን አልሰማቸውም። 7. በረዶ 13 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም እንዲህም በለው፦ የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14 በዚህ ጊዜ መቅሠፍቴን ለልብህ በአገልጋዮችህ በሕዝብህም በምድር ሁሉ ላይ እልካለሁ ይህም እንደ እኔ ያለ እንደሌለ እንድታውቅ ነው። 15 አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን በተላላፊ በሽታ በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ 16 ነገር ግን እንድትቆም ያደረግኩት ኃይሌን እንድገልጥብህና ስሜም በምድር ሁሉ ላይ እንዲታወጅ ነው። 17 እንዳትለቅቃቸው አሁንም በሕዝቤ ላይ ትታበያለህ፤ 18 እነሆ እኔ ነገ በዚህ ጊዜ በግብጽ፥ ከተመሠረተች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ከባድ በረዶ አዘንባለሁ። 19 ስለዚህም ልከህ ከብቶችህንና በሜዳ ያለ የአንተ የሆነውን ሁሉ አምጣ፤ በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንሰሳ ሁሉ ላይ በረዶ ይወርዳል እነርሱም ይሞታሉ።’” 20 ከፈርዖን አገልጋዮች የጌታን ቃል የፈራ አገልጋዮቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤ 21 የጌታንም ቃል በልቡ ያላስቀመጠ አገልጋዮቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ። 22 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ በሰው፥ በከብት፥ በእርሻ ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብጽ ምድር ሁሉ በረዶ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ።” 23 ሙሴም በትሩን ወደ ሰማያት ዘረጋ፤ ጌታም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ ጌታም በግብጽ ምድር ላይ በረዶ አዘነበ። 24 በረዶና እሳት ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እጅግ ከባድ የሚበርቅ እሳት ነበር፥ በግብጽ ምድር ሁሉ አገር ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ሆኖ አያውቅም። 25 በረዶውም በግብጽ ምድር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ከሰው እስከ እንስሳ መታ፤ የእርሻን ቡቃያ መታ፥ በረዶውም የአገሩን ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 26 የእስራኤል ልጆች በነበሩባት በጎሼን ምድር ብቻ በረዶ አልነበረም። 27 ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በዚህ ጊዜ ኃጢአትን ሰርቻለሁ፤ ጌታ ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም በደለኞች ነን። 28 የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ ጌታ ጸልዩ፤ እለቅቃችኋለሁ፥ ከዚህ በኋላ እዚህ አትቀመጡም።” 29 ሙሴም እንዲህ አለው፦ “ከከተማ እንደ ወጣሁ እጄን ወደ ጌታ እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ የጌታ እንደ ሆነች እንድታውቅ፥ ነጎድጓዱ ይቆማል፥ በረዶውም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። 30 አንተና አገልጋዮችህ ጌታ አምላክን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁና።” 31 ገብሱና ተልባው ተመታ፤ ገብሱ ገና እሸት ተልባውም እንቡጥ ስለ ነበረ ነው። 32 ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም። 33 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ ጌታ ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ቆመ፥ ዝናቡም ወደ ምድር አልዘነበም። 34 ፈርዖንም ዝናቡ፥ በረዶውና ነጎድጓዱ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ ኃጢአትን ጨመረ፥ እርሱና አገልጋዮቹም ልባቸውን አደነደኑ። 35 የፈርዖንም ልብ ጸና፤ ጌታም በሙሴ አፍ እንደ ተናገረ የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም። |