Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፀአት 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የእስራኤል ከግብፃውያን አርነት መውጣት እንደ ተረጋገጠ

1 ጌታም ሙሴን አለው፦ “አሁን ፈርዖንን ምን እንደማደርገው ታያለህ በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋል፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋል።”

2 እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤

3 ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብም ሁሉን የሚችል አምላክ ሆኜ ተገለጥኩላቸው፤ ጌታ የሚለውን ስሜን ግን አላስታወቅኳቸውም።

4 ደግሞም የከነዓንን ምድር፥ በእንግድነት ተቀምጠውበት የነበረውን የእንግድነታቸው ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን መሰረትኩ።

5 ደግሞም እኔ ግብፃውያን እንዲሰሩ የሚያስገድዷቸውን የእስራኤልን ልጆች ጩኸት ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።

6 ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ጌታ ነኝ፥ ከግብፃውያን ጭቆና አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታችሁም አላቅቃችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድ በታላቅ የፍርድ ሥራም አድናችኋለሁ፤

7 ለእኔ ሕዝብ አድርጌ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብጽ ጭቆና ያወጣኋችሁ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

8 ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ እሰጣታለሁ ብዬ እጄን ወደ አነሳሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ እርሷንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።’”

9 ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከመንፈሳቸው መሰበር ከከባዱም ሥራ የተነሣ ሙሴን አልሰሙትም።

10 ጌታም ሙሴን አለው፦

11 “ግባ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከምድሩ እንዲለቅ ንገረው።”

12 ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ ታድያ እንዴት ፈርዖን ይሰማኛል? እኔ ደግሞ ከንፈሬ ያልተገረዘ ሰው ነኝ” ብሎ ተናገረ።

13 ጌታም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የእስራኤልን ልጆችንና የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ እንዲያወጣቸው እንዲነግሩት አዘዛቸው።


የሙሴና የአሮን ትውልድ

14 የአባቶቻቸው ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል ልጆች ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔፅሮንና ካርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው።

15 የስምዖንም ልጆች ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሻኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው።

16 እነዚህ የሌዊ ልጆች ስሞች እንደ ትውልዳቸው ጌርሾን፥ ቀሃት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።

17 የጌርሾንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሊብኒና፥ ሽምኢ ናቸው።

18 የቀሃትም ልጆች ዓምራም፥ ይፅሃር፥ ሔብሮን፥ ዑዚኤል ናቸው፤ የቀሃትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው።

19 የሜራሪ ልጆች ማሕሊ፥ ሙሺ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው።

20 ዓምራምም የአባቱን እኅት ዮካቤድን አገባ፥ አሮንንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የዓምራምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።

21 የይፅሃር ልጆች ቆራሕ፥ ኔፌግ፥ ዚክሪ ናቸው።

22 የዑዚኤል ልጆች ሚሻኤል፥ ኤልጻፋን፥ ሢትሪ ናቸው።

23 አሮንም የዓሚናዳብን ልጅ የናሕሾንን እኅት ኤሊሼባን አገባ፥ እርሷም ናዳብ፥ አቢሁ፥ ኤልዓዛርንና ኢታማርን ወለደችለት።

24 የቆራሕ ልጆች አሲር፥ ኤልቃናና፥ አቢያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆራሓውያን ወገኖች ናቸው።

25 የአሮንም ልጅ ኤልዓዛር ከፑቲኤል ልጆች አንዷን ሚስት አገባ፥ እርሷም ፒንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው።

26 እነዚህ አሮንና ሙሴ ጌታ፦ “የእስራኤልን ልጆች በየነገዳቸው ከግብጽ ምድር አውጡ” ያላቸው ናቸው።

27 እነዚህ ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ስለማውጣት የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህም ሙሴና አሮን ናቸው።


እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን የሰጠው ትእዛዝ

28 ጌታ በግብጽ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን፥

29 እርሱም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እኔ የምነግርህን ሁሉ ንገረው።”

30 ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ እኔ ከንፈሬ ያልተገረዘ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል?” አለ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos