ዘፀአት 39 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለክህነት የሚሆኑ ልብሶች አሠራር 1 በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ በብልሃት የተሠራ ልብስ አደረጉ፥ ጌታም ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ። 2 ኤፉዱንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራ። 3 ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቆረጡት። ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራው በሰማያዊው፥ በሐምራዊው፥ በቀዩ ግምጃ፥ በተፈተለው ጥሩ በፍታ መካከል በእርሱ ጠለፉ። 4 እንዲጋጠም በሁለቱ ትከሻዎች ላይ መጋጠሚያ ሠሩለት፥ በሁለቱ ጫፎች እንዲጋጠም አደረጉት። 5 በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ፥ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ከእርሱ ጋር ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር። 6 በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። 7 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች እንዲሆኑ በኤፉዱ በትከሻው ላይ አደረጋቸው። 8 የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሠራው እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው። 9 አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱንም ኪስ ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ አንድ ስንዝር፥ ወርዱም አንድ ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። 10 በእርሱም ላይ በአራት ረድፍ ዕንቁዎቹን አደረጉበት፤ በመጀመሪያ ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ 11 በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና አልማዝ፤ 12 በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፤ 13 በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ። 14 የዕንቁዎቹም ድንጋዮች እንደ ዐሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፥ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ ዐሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። 15 ለደረቱ ኪስም እንደ ገመድ የተጐነጐኑ ድሪዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ። 16 ሁለት የወርቅ ፈርጦችና ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ በኩል አደረጉት። 17 ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ጫፎች ባሉት በሁለቱ ቀለበቶች አስገቡ። 18 የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ። 19 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችንም ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው። 20 ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከትከሻዎቹ በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው። 21 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ፈትል አሰሩት። 22 የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ሠራው። 23 በቀሚሱ መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም አንገትጌው ዙሪያውን ተጠልፎ ነበር። 24 በቀሚሱ ታችኛው ዘርፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ በፍታ ሮማኖችን አደረጉ። 25 ከንጹሕ ወርቅ ሻኩራዎችን ሠሩ፥ ሻኩራዎቹንም በሮማኖቹ መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። 26 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ለማገልገል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኩራና ሮማን፥ ሻኩራና ሮማን አደረጉ። 27 የሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ቀሚስ አዘጋጁ፥ 28 ከጥሩ በፍታ መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም ቆቦች፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ፥ 29 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተጠለፈ መታጠቂያ ሠሩ። 30 የተቀደሰውን አክሊል አበባ ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም “ለጌታ የተቀደሰ” የሚል ጽሑፍ ቀረጹበት። 31 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው በመጠምጠሚያው ላይ እንዲያንጠለጥሉት ሰማያዊ ፈትል አሰሩበት። የሥራው ፍጻሜ 32 የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጠናቀቀ። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ልክ እንደዛው አድርገው ሠሩ፤ እንዲሁ አደረጉ። 33 ማደሪያውን ወደ ሙሴ አመጡት፥ ድንኳኑን፥ የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ፥ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንና እግሮቹን፥ 34 ከቀይ አውራ በግ ቁርበት የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበት የተሠራ መደረቢያ፥ መሸፈኛ መጋረጃ፥ 35 የምስክሩን ታቦት፥ መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውን፥ 36 ገበታውንና ዕቃውን ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹን፥ 37 ንጹሑን መቅረዝ፥ መብራቶቹን፥ የተደረደሩትን ቀንዲሎችና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ፥ የመብራቱን ዘይት፥ 38 የወርቁን መሠዊያ፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፥ የድንኳኑን ደጃፍ መጋረጃ፥ 39 የናሱን መሠዊያ፥ የናሱን መከታ፥ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫው፥ 40 የአደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹን፥ እግሮቹን፥ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹን፥ ካስማዎቹን፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ 41 በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም እንዲያገለግሉበት የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶችና የልጆቹን ልብሶች አመጡ። 42 የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ ልክ እንደዛው አድርገው ሠሩ። 43 ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆ ልክ ጌታ እንዳዘዘው አድርገውት ነበር፤ እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው። |