ዘፀአት 37 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የቃል ኪዳኑ ታቦት አሠራር 1 ባስልኤል ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 2 ውስጡንና ውጪውን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገለት። 3 በአራቱ እግሮቹ ላይ አራት የወርቅ ቀለበቶችን አደረገለት፤ በአንድ በኩል ሁለት ቀለበቶችን፥ በሌላው በኩል ሁለት ቀለበቶች ሆኑ። 4 መሎጊያዎችን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 5 ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አስገባ። 6 ከንጹሕ ወርቅ የስርየት መክደኛ ሠራ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 7 ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሁለት ኪሩቤል ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ላይ በሁለቱ ጫፎች አደረጋቸው። 8 አንዱን ኪሩብ በዚህኛው በኩል፥ አንዱን ኪሩብ በዚያኛው በኩል አደረጋቸው፥ በሁለቱ ጫፎች ከስርየት መክደኛው ሠራቸው። 9 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ነበሩ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ትይዩ ነበሩ፥ የኪሩቤል ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ይመለከት ነበር። ለፊቱ ሕብስት የሚሆን ገበታ አሠራር 10 ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ። 11 በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገለት። 12 በዙሪያው አንድ ስንዝር የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅ አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት። 13 አራት የወርቅ ቀለበቶችን አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮች ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ። 14 ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አጠገብ ነበሩ። 15 ገበታውን እንዲሸከሙባቸው መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16 በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎችን፥ ጽዋዎችንና ለማፍሰሻ የሚሆኑ መቅጃዎችን፥ ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። የመቅረዙ አሠራር 17 መቅረዙን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጉብጉቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ። 18 በጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ በኩል፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ በኩል። 19 በአንደኛው ቅርንጫፍ እንቡጥ፥ ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ እንቡጥ፥ ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ። 20 በመቅረዙም ጉብጉቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ። 21 ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጉብጉብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጉብጉብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጉብጉብ ነበረ። 22 ጉብጉቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር። 23 ሰባቱን መብራቶቹን፥ መኰስተሪያዎቹንና የኩስታሪ ማድረጊያዎቹን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። 24 መቅረዙንና ዕቃዎቹን ሁሉ ከአንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ሠራ። የዕጣን መሠዊያው አሠራር 25 የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 26 ላዩን፥ የጎኑን ዙሪያ በሙሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት። 27 ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በሁለቱም ጎን በሁለቱም ማዕዘን አደረጋቸው፥ ለመሸከምም የመሎጊያዎቹ ስፍራ ነበሩ። 28 መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። የቅባቱ ዘይትና የዕጣኑ አዘገጃጀት 29 የተቀደሰ የቅባት ዘይት፥ ንጹሕና መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን ቀማሚ እንደሚሠራው አደረገ። |