ዘፀአት 36 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ባስልኤል፥ ኤልያብና ጥበበኞች ሁሉ፥ የመቅደሱን አገልግሎት ሥራ ሁሉ እንዲያደርጉና እንዲያውቁ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ጌታ ያዘዘውን ነገር ሁሉ አደረጉ። 2 ሙሴም ባስልኤልን፥ ኤልያብንና ጌታ በልቡ ጥበብን ያሳደረበትን ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውን ለመሥራት ልቡ ያነሣሣውን ሁሉ ጠራቸው። 3 የመቅደሱን ሥራ ለመሥራት የእስራኤል ልጆች ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ወሰዱ። እነዚያም በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ስጦታ አሁንም ማለዳ ማለዳ ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። 4 የመቅደሱን ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፥ 5 ሙሴንም፦ “ሕዝቡ ጌታ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ አመጡ” አሉት። 6 ሙሴም በሰፈሩ ውስጥ አዋጅ እንዲተላለፍ አዘዘ፦ “ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ስጦታ ከእንግዲህ ወዲህ አያምጣ”፤ ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ። 7 ያመጡት ነገር ሥራውን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ይተርፍ ነበር። የድንኳኑ አሠራር 8 ሥራ ሲሠሩ ከነበሩት ጥበበኞች የሆኑት ሁሉ ማደሪያውን ሠሩ፤ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ፥ ኪሩቤልም የተጠለፈባቸው ዐሥር መጋረጃዎች ሠሩ። 9 የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የሁሉም መጋረጃዎች መጠን እኩል ነበር። 10 አምስቱን መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አጋጠመ፥ ሌሎቹንም አምስት መጋረጃዎች እንዲሁ እርስ በርሳቸው አጋጠመ። 11 በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ በመጋጠሚያው ላይ የሰማያዊው ግምጃ ቀለበቶች አደረገ፤ ደግሞ በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በመጋጠሚያው ላይ እንዲሁ አደረገ። 12 አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው መጋረጃ አደረገ፥ አምሳ ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ መጋጠሚያ አደረገ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ። 13 አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሠራ፤ መጋረጆችንም እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጠማቸው፤ ማደሪያውም አንድ ወጥ ሆነ። 14 ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን መጋረጃዎችን ከፍየል ጠጉር ሠራ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠራ። 15 የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሠላሳ ክንድ፥ የእያንዳንዱም መጋረጃ ወርድ አራት ክንድ ነበረ፤ የዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች መጠን እኩል ነበረ። 16 አምስቱን መጋረጃዎች አንድ ላይ ለብቻ፥ ስድስቱንም መጋረጃዎች አንድ ላይ ለብቻ አድርጎ አጋጠማቸው። 17 ከተጋጠሙት መጋረጃዎች በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረገ፤ እንዲሁም በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በሚጋጠሙበት በኩል አምሳ ቀለበቶች አደረገ። 18 ድንኳኑ አንድ ወጥ እንዲሆን የሚያጋጥሙበት አምሳ የነሐስ መያዣዎችን ሠራ። 19 ለድንኳኑ መሸፈኛ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ በላዩ ላይ የሚሆን መሸፈኛ ከአቆስጣ ቁርበት ሠራስስ። 20 ለማደሪያው የሚቆሙ ሳንቃዎችን ከግራር እንጨት ሠራ። 21 የእያንዳንዱ ሳንቃ ርዝመት ዐሥር ክንድ፥ ወርድ አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 22 እያንዳንዱ ሳንቃ አንዱ በአንዱ ላይ የሚያያዝበት ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩት፤ ለማደሪያው ሳንቃዎች በሙሉ እንዲሁ አደረገ። 23 ለማደሪያው ሳንቃዎችን አደረገ፤ በደቡብ በኩል ሃያ ሳንቃዎችን አደረገ፤ 24 ከሃያው ሳንቃዎች በታች አርባ የብር እግሮችን አደረገ፤ በአንደኛው ሳንቃ ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች፥ በሁለተኛው ሳንቃ ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች አደረገ። 25 ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሃያ ሳንቃዎችን አደረገ፤ 26 አርባ የብር እግሮች፥ ከአንዱ ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች፥ ከአንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረገ። 27 በማደሪያው በስተ ኋላ በምዕራብ በኩል ስድስት ሳንቃዎችን አደረገ። 28 በማደሪያው በሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቃዎችን አደረገ። 29 ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ። 30 ስምንት ሳንቃዎች ነበሩ፥ የብር እግሮቻቸውም ዐሥራ ስድስት እግሮች ነበሩ፥ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ነበሩ። 31 ከግራር እንጨት መወርወሪያዎችን ሠራ፥ በማደሪያው በአንደኛው በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት፥ 32 በማደሪያው በሁለተኛው በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ ከማደሪያው በስተ ኋላ በምዕራቡ በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎችን ሠራ። 33 በመካከል ያለውን መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲያልፍ አደረገ። 34 ሳንቃዎቹን በወርቅ ለበጣቸው፥ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያው ማስገቢያ እንዲሆኑ ከወርቅ ሠራ፥ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጣቸው። 35 መጋረጃውንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ሠራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሠራው ኪሩቤልን በእርሱ ላይ አደረገ። 36 አራት ምሰሶዎችን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኩላቦቻቸው የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች ሠራላቸው። 37 ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተጠለፈ መጋረጃ አደረገ፤ 38 አምስቱን ምሰሶዎችንና ኩላቦቻቸውን አደረገ፤ ጉልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውን በወርቅ ለበጣቸው፥ አምስቱ እግሮቻቸው የነሐስ ነበሩ። |