ዘፀአት 33 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ከሲና እንዲወጡ የተሰጠ ትእዛዝ 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሂድ፥ አንተ ከግብጽ ምድር ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’ ብዬ ወደ ማልሁባት ምድር ውጣ፤ 2 በፊትህ መልአክ እልካለሁ፥ ከነዓናዊውን፥ አሞራዊውን፥ ኬጢያዊውን፥ ፌርዛዊውን፥ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን አወጣልሃለሁ። 3 ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ምድር ውጣ፤ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆንክ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ ከአንተ ጋር አልወጣም።” 4 ሕዝቡ ይህን ክፉ ወሬ ሰምተው አዘኑ፤ ከእነርሱም ማንም ጌጡን አላደረገም። 5 ጌታም ሙሴን፦ “ለእስራኤል ልጆች ‘እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፥ አንድ ጊዜ ከእናንተ ጋር ብወጣ አጠፋችኋለሁ፤ አሁንም በእናንተ ላይ የማደርገውን እንዳውቅ ጌጣችሁን አውጡ’ በላቸው አለው።” 6 የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ጌጣቸውን አወለቁ። የመገናኛው ድንኳን 7 ሙሴ ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈሩ ራቅ አድርጎ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ “የመገናኛ ድንኳን” ብሎ ጠራው። ጌታን የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። 8 ሙሴ ወደ ድንኳኑ በሚሄድበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆምና ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። 9 ሙሴ ወደ ድንኳኑ በሚገባበት ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፤ ጌታም ሙሴን ያናግረው ነበር። 10 ሕዝቡ ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ይሰግድ ነበር። 11 ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ጌታም ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴ ወደ ሰፈሩ ሲመለስ አገልጋዩ የሆነው ወጣቱ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። የሙሴ ልመና 12 ሙሴ ጌታን እንዲህ አለው፥ “እይ! አንተ ‘ይህን ሕዝብ አውጣ’ ብለኸኛል፥ ነገር ግን ከእኔ ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም፦ ‘በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር። 13 አሁንም በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ እንዳውቅህና በፊትህም ሞገስን እንዳገኝ እባክህ መንገድህን አሳየኝ፤ ይህንንም ሕዝብ እንደ ሕዝብህ እየው።” 14 እርሱም “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው። 15 ሙሴም እንዲህ አለው፦ “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ ከዚህ አታውጣን። 16 እኔና ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? እኔና ሕዝብህ በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ የተለየን የምንሆነው አንተ ከእኛ ጋር በመውጣትህ አይደለምን?” 17 ጌታ ሙሴን፦ “በፊቴ ሞገስን ስላገኘህና በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ” አለው። 18 እርሱም፦ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለ። 19 እርሱም እንዲህ አለው፦ “እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ የጌታንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውን እምራለሁ።” 20 ደግሞም “ሰው አይቶኝ መኖር አይችልምና ፊቴን ማየት አትችልም” አለ። 21 ጌታ እንዲህ አለው፦ “እነሆ የምትቆምበት ስፍራ በአጠገቤ አለ፥ በዓለቱ ላይ ትቆማለህ፤ 22 ክብሬ ሲያልፍ ዓለቱ ስንጥቅ ውስጥ አስቀምጥሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ በመዳፌ እጋርዳለሁ፤ 23 መዳፌን አነሣለሁ፥ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።” |