Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፀአት 32 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የወርቅ ጥጃው ምስል

1 ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፦ “ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ ተነሥና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን” አሉት።

2 አሮንም፦ “በሚስቶቻችሁ፥ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

3 ሕዝቡ ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት።

4 ከእጃቸው ተቀብሎ በቅርጽ መሥሪያ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃ አደረገው፤ እርሱም፦ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” አላቸው።

5 አሮንም አየውና መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፦ “ነገ የጌታ በዓል ነው” ሲል አወጀ።

6 በማግስቱ ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የሰላም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ።

7 ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ ውረድ፤

8 ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ለራሳቸውም ቀልጦ የተሠራ ጥጃ ሠሩ፥ ሰገዱለት፥ ሠዉለትም፦ ‘እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው’ አሉ።”

9 ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው።

10 አሁንም ቁጣዬ በእነርሱ ላይ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከአንተም ታላቅ ሕዝብ አደርጋለሁ።”

11 ሙሴም በጌታ አምላኩ ፊት ለመነ፥ እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብጽ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ቁጣህ ስለምን ነደደ?

12 ግብፃውያን ‘በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከገጸ ምድር ሊያጠፋቸው ለክፋት ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከቁጣህ መዓት ተመለስ፥ በሕዝብህ ጥፋት ላይ ራራ።

13 ‘ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም ምድር ሁሉ እንደተናገርሁት ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል’ ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባርያዎችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና እስራኤልን አስብ።”

14 ጌታም በሕዝቡ ላይ አደርጋለሁ ያለውን ክፋ ነገር መለሰ።

15 ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር።

16 ጽላቶቹ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፥ በጽላቶቹ ላይ የተቀረው ጽሑፍም የእግዚአብሔር ጽሑፍ ነበረ።

17 ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፦ “የጦርነት ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ” አለው።

18 እርሱም፦ “ይህ የድል ነሺዎች ድምጽ ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ” አለው።

19 እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንና ዘፈኑን አየ፤ የሙሴ ቁጣ ነደደ፥ ጽላቶቹን ከእጁ ወርውሮ ከተራራው በታች ሰበራቸው።

20 የሠሩትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እስኪደቅም ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲጠጡት አደረገ።

21 ሙሴም አሮንን፦ “ይህንን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ?” አለው።

22 አሮንም እንዲህ አለ፦ “የጌታዬ ቁጣ አይንደድ፤ ይህ ሕዝብ ክፋ እንደሆነ አንተ ታውቃለህ።

23 እነርሱም፦ ‘ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን’ አሉኝ።

24 እኔም፦ ‘ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ሁሉ ሰብሮ ያምጣልኝ’ አልኋቸው፤ እነርሱም ሰጡኝ፥ በእሳት ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ።”

25 ሙሴ በጠላቶቻቸው ፊት መሳለቂያ እንዲሆኑ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥

26 ሙሴ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ፦ “የጌታ ወገን የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ!” አለ፤ የሌዊ ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።

27 እንዲህም አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እያንዳንዱ ሰው ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩ ውስጥ ከበር እስከ በር ወዲህ ወዲያ ተመላለሱ፥ ሰው ሁሉ ወንድሙን፥ ሰው ሁሉ ወዳጁን፥ ሰው ሁሉ ጎረቤቱን ይግደል’”

28 የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያ ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ።

29 ሙሴም “ዛሬ በላያችሁ ላይ በረከት እንዲያወርድ እያንዳንዱ በልጁና በወንድሙ ላይ ተነሥቷልና ዛሬ ለጌታ እጃችሁን ቀደሳችሁ” አለ።

30 በማግስቱም ሙሴ ለሕዝቡ “እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ ጌታ እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ ይሆናል” አላቸው።

31 ሙሴም ወደ ጌታ ተመልሶ “ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤

32 አሁንም ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፥ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ” አለ።

33 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ።

34 አሁንም ሂድ፥ ይህንንም ሕዝብ ወደ ነገርኩህ ስፍራ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን በላያቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ።”

35 አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ ጌታ ሕዝቡን ቀሠፈ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos