Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፀአት 31 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ባስልኤልና ኤልያብ

1 ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦

2 “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ።

3 በጥበብ፥ በማስተዋል፥ በእውቀትና ሥራ ሁሉ እንዲሠራ የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፥

4 ልዩ ማስተዋል እንዲኖረው፥ በወርቅ፥ በብርና በነሐስ እንዲሠራ፥

5 ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ እንዲቀርጽ፥ እንጨት እንዲጠርብ፥ ሁሉንም ሥራ እንዲሠራ ሞላሁበት።

6 እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሆነውን የአሒሳማክን ልጅ ኤልያብን ሰጥቼዋለሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ እንዲያደርጉ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ላይ ጥበብን አኑሬአለሁ።

7 የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩን ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑን ዕቃ በሙሉ፥

8 ገበታውና ዕቃው ሁሉ፥ ንጹሑን መቅረዝና ዕቃውን፥ የዕጣን መሠዊያውን፥

9 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያ ሳሕንና መቀመጫውን፥

10 በብልሃት የተሠራውን ልብስ፥ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑ የአሮን የተቀደሱ ልብሶች የልጆቹ ልብሶች፥

11 የቅባቱን ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ እንዲሁ ያድርጉ።”


የሰንበት ሕግ

12 ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦

13 “አንተ ግን ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ፥ ይህ የምቀድሳችሁ ጌታ እኔ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ለትውልዶቻችሁ ምልክት ነውና።

14 ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰው ፈጽሞ ይገደል፥ በእርሷ ሥራን የሚሠራ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።

15 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል።

16 የእስራኤል ልጆች ሰንበትን ይጠብቁ፤ ሰንበትን መጠበቅ ለትውልዳቸው የዘለዓለም ቃል ኪዳን ያድርጉት።

17 በእኔና በእስራኤል ልጆች መካከል የዘለዓለም ምልክት ነው፤ ጌታ ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ፈጥሮአልና፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው አርፎአልና፥ ተነቃቅቶአልና።’”


ሁለቱ የኪዳን ጽላቶች

18 በሲና ተራራ ከሙሴ ጋር ንግግሩን ከፈጸመ በኋላ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች የሆኑ ሁለት የምስክር ጽላቶችን ሰጠው።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos