ዘፀአት 28 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የክህነት ልብስ አሠራር 1 ወንድምህን አሮንንና ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት እንዲሆኑልኝ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፥ አቢሁን፥ አልዓዛርንና ኢታማርን አቅርብ። 2 ለክብርና ለውበት እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሰ ልብስ ሥራለት። 3 ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ እንዲሆን ለአሮን ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። 4 የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፥ ኤፉድ፥ ቀሚስ፥ የተጠለፈ እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያና መታጠቂያ፤ ካህን እንዲሆንልኝ ለወንድምህ ለአሮንና ለልጆቹ የተቀደሰ ልብስ ይሥሩላቸው። 5 ወርቅ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊ፥ ቀይም ግምጃና ጥሩ በፍታም ይውሰዱ። ኤፉዱ 6 “ኤፉዱንም በወርቅ፥ በሰማያዊ፥ በሐምራዊ፥ በቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በብልሃት የተሠራ ይሁን። 7 ሁለቱ ወገን አንድ ሆኖ እንዲጋጠም በሁለቱ ትከሻ ላይ የሚጋጠም ይሁን። 8 በላዩ ያለው በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ መታጠቂያ ከእርሱ ጋር ወጥ ሆኖ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተሠራ ይሁን። 9 ሁለት የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ቅረጽባቸው፤ 10 እንደ የልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ ላይ፥ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላኛው ድንጋይ ቅረጽ። 11 በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ በወርቅ ፈርጥ ሥራቸው። 12 የእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች እንዲሆኑ ሁለቱን ዕንቁዎች በኤፉዱ ትከሻዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ትከሻዎቹ ላይ ለመታሰቢያ እንዲሆን ስማቸውን በጌታ ፊት ይሸከማል። 13 ፈርጦችን ከወርቅ ሥራ፤ 14 እንደ ተጎነጎነ ገመድ አድርገህ ሁለት ድሪዎች ከንጹሕ ወርቅ ሥራ፤ የተጎነጎኑትንም ድሪዎች ከፈርጦቹ ጋር አያይዛቸው። የደረት ኪስ አሠራር 15 “የፍርዱን የደረት ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራው ሥራው፤ እንደ ኤፉዱ አሠራር ሥራው፤ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከጥሩ በፍታ ሥራው። 16 ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ አራት መዕዘንና ድርብ ይሁን። 17 አራት ረድፍ የሆነ የዕንቁ ፈርጥ አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ 18 በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና አልማዝ፤ 19 በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጦኖስ፤ 20 በአራተኛው ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፤ በወርቅ ፈርጥ ይቀመጣሉ። 21 የዕንቁ ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ዐሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ማኅተም እንደሚቀረጽ በየስማቸው ይቀረጹ። 22 ለደረት ኪሱም የተጎነጎኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከንጹሕ ወርቅ ሥራቸው። 23 ለደረት ኪሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሥራ፥ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረት ኪሱ በሁለቱ ጫፎች አድርጋቸው። 24 ሁለቱ የተጎነጎኑ የወርቅ ድሪዎችን በደረቱ ኪስ ጫፎች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታስገባቸዋለህ። 25 የሁለቱን ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ትከሻ በፊት ለፊት ታደርጋቸዋለህ። 26 ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረት ኪሱ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። 27 በተጨማሪም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ በኤፉዱም ፊት ለፊት ከትከሻዎቹ በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። 28 የደረት ኪሱም በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ፥ የደረት ኪሱን ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያያይዙታል። 29 አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ ዘወትር መታሰቢያ እንዲሆን በጌታ ፊት የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ ደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። 30 በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፥ በጌታ ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በጌታ ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል። ሌሎች የክህነት ልብሶች 31 “የኤፉዱን መደረቢያ ሙሉ ሰማያዊ አድርገው። 32 መሃሉ ላይ ራስ ማስገቢያ አንገትጌ ይኑረው፤ እንዳይቀደድም የአንገትጌው ዙሪያ የተጠለፈ ይሁን። 33 በታችኛው ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያም መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኩራዎች አድርግ፤ 34 የወርቅ ሻኩራና ሮማን፥ የወርቅ ሻኩራና ሮማን በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። 35 በአገልግሎት ጊዜ በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በጌታ ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል። 36 ከንጹህ ወርቅ ቅጠል ሥራ፥ በእርሱም ላይ እንደ ማኅተም ቅርጽ ‘ለጌታ የተቀደሰ’ የሚል ቅረጽበት። 37 በመጠምጠሚያው ፊት በሰማያዊ ፈትል በመጠምጠሚያው ላይ ስፋው። 38 በአሮን ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በጌታ ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠሉ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን። 39 እጀ ጠባቡን ከጥሩ በፍታ፥ መጠምጠሚያውን ከበፍታ ትሠራለህ፥ በጥልፍ የተጠለፈ መታጠቂያ ትሠራለህ። 40 ለአሮን ልጆች እጀ ጠባቦችን፥ መታጠቂያዎችንና ቆቦችን ለክብርና ለጌጥ ትሠራላቸዋለህ። 41 ወንድምህን አሮንንና ከእርሱም ጋር ልጆቹን እነዚህን አልብሳቸው፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ እጆቻቸውንም ታነጻለህ፥ ትቀድሳቸዋለህም። 42 ኀፍረተ ሥጋቸውን እንዲሸፍኑበት ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ 43 ኃጢአት እንዳይሆንባቸውና እንዳይሞቱ፥ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ ወይም በመቅደሱ ሊያገለግሉ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናሉ፤ ለእርሱና ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል። |