ዘፀአት 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለእግዚአብሔር ቤት የሚቀርብ መባ 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “መባ እንዲያመጡልኝ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፤ በፈቃዱ ሊሰጠኝ ልቡ ከተነሣሣ ሰው ሁሉ መባዬን ተቀበሉ። 3 ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፦ ወርቅ፥ ብርና ናሐስ፥ 4 ሰማያዊ፥ ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታና የፍየል ጠጉር፥ 5 ቀይ የተለፋ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአስቆጣ ቁርበት፥ የግራር እንጨት፥ 6 ለመብራት የሚሆን ዘይት፥ ለቅባት የሚሆን ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን የሚሆን ቅመም፥ 7 መረግድ፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ። 8 በመካከላቸው እንድኖር መቅደስ ይሥሩልኝ። 9 እኔ እንዳሳየሁህ ሁሉ፥ እንደ ድንኳኑ ምሳሌ፥ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። የቃል ኪዳኑ ታቦት 10 “ከግራር እንጨት ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 11 ውስጡንና ውጪውም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በላዩ ላይ ዙሪያውን ሁሉ የወርቅ አክሊል አድርግለት። 12 አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። 13 ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 14 ታቦቱን በእነርሱ ለመሸከም በታቦቱ ጎን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አስገባ። 15 መሎጊያዎቹ በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከዚያም አይውጡ። 16 እኔ የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር። 17 ከንጹሕ ወርቅ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። 18 ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። 19 አንዱን ኪሩብ በአንድ በኩል፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው በኩል አኑር፥ በስርየት መክደኛው ላይ ኪሩቤል በሁለት በኩል ላይ ታደርጋቸዋለህ። 20 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። 21 የስርየት መክደኛውን በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔ የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። 22 በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች እንድታዝዝ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ። ለፊቱ ኅብስት የሚሆን ገበታ 23 “ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ። 24 በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤ 25 በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት። 26 አራት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች ላይ አድርጋቸው። 27 ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ። 28 ገበታውን እንዲሸከሙባቸው መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 29 ለማፍሰሻም እንዲሆኑ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው። 30 በገበታው ላይ ኅብስተ ገጹን ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ። መቅረዙ 31 “ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ ሥራ፤ መቅረዙ የተቀጠቀጠ ሥራ ይሁን፤ እግሩና ከአገዳው ጋር ጽዋዎቹም ጉብጉቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት። 32 በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ። 33 በአንደኛው ቅርንጫፍ እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች አድርግ፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ። 34 በመቅረዙም እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ አራት ጽዋዎች ይኑሩት። 35 ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ እንቡጥ፥ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ እንቡጥ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ እንቡጥ ይሁን። 36 እንቡጦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ይሁኑ፤ ሁሉም ወጥ ሆኖ ከተቀጠቀጠ ከንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። 37 ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊት ለፊት እንዲያበሩ መብራቶቹን ከፍ አድርገህ አስቀምጣቸው። 38 መኮስተሪያዎችዋንና የኩስታሪ ማስቀመጫዎችዋን ከንጹሕ ወርቅ ሥራ። 39 እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ከአንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። 40 በተራራው ላይ ባሳየሁህ ምሳሌ መሠረት ለመስራት ጥንቃቄ አድርግ።” |