ዘፀአት 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ስለ ባርያዎች የተሰጠ ሕግ 1 “በፊታቸው የምታኖረው ሥርዓት ይህ ነው። 2 ዕብራዊ ባርያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛው ዓመት ግን እንዲሁ ነፃ ይውጣ። 3 ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ። 4 ጌታው ሚስት ሰጥቶት ከሆነ እና ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታዋ ይሁኑ፥ እርሱ ብቻውን ይውጣ። 5 ባርያውም፦ ጌታዬን፥ ሚስቴንና ልጆቼን እወድዳለሁ፥ ነፃ አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ 6 ጌታው ወደ እግዚአብሔር ያቅርበው፥ ወደ በሩ ወይም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘለዓለምም ያገልግለው። 7 “አንድ ሰው ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ወንድ ባርያዎች እንደሚወጡ አትውጣ። 8 ጌታዋን ደስ ባታሰኘው እንድትዋጅ ይስጣት፤ በድሎአታልና ለባዕድ ሕዝብ ሊሸጣት መብት የለውም። 9 ለልጁም ሊድራት ቢፈልግ፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት። 10 ሌላይቱን ቢያገባ፥ ምግብዋን፥ ልብስዋንና የጋብቻ መብቷን አይቀንስባት። 11 እነዚህንም ሦስት ነገሮች ባያደርግላት፥ ያለ ገንዘብ ትውጣ። ስለ ዐመፅ የተሰጠ ሕግ 12 “ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ ፈጽሞ ይሙት። 13 ሳይሸምቅበት፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አዘጋጅልሃለሁ። 14 ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውንም በተንኮል ቢገድለው፥ እንዲገደል ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው። 15 አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይሙት። 16 ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ ፈጽሞ ይሙት። 17 አባቱን ወይም እናቱን የሚያዋርድ ፈጽሞ ይሙት። 18 “ሰዎች ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ ቢመታው፥ ባይሞት ነገር ግን በአልጋ ላይ ቢውል፥ 19 ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ውጭ ቢወጣ፥ ሥራ ስላስፈታው ገንዘብ ከመክፈልና፥ እስኪፈወስም ድረስ ከማሳከም በቀር የመታው ሰው ከወንጀል ነጻ ነው። 20 አንድ ሰው ወንድ ባርያውን ወይም ሴት ባርያውን በበትር ቢመታ፥ በእጁም ቢሞትበት፥ ያው ቅጣት ይቀጣ። 21 ነገር ግን የተመታው አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቆይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ። 22 ሰዎች ሲጣሉ፥ ያረገዘችን ሴት ቢመቱ ቢያስወርዳት ነገር ግን እርስ ባትጎዳ፥ የሴቲቱ ባል የጣለበትን ያህል ካሳ ይክፈል፤ ይህም በዳኞቹ ይሰጥ። 23 ጉዳት ቢደርስባት ግን ሕይወት ስለ ሕይወት፥ 24 ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ሰለ ጥርስ፥ እጅ ስለ እጅ፥ እግር ስለ እግር፥ 25 መቃጠል ስለ መቃጠል፥ ቁስል ስለ ቁስል፥ ግርፋት ስለ ግርፋት ይክፈል። 26 አንድ ሰው የባርያውን ወይም የባርያይቱን ዐይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ በነጻ ይልቀቀው። 27 የባርያውን ወይም የባርያይቱን ጥርስ ቢያወልቅ፥ ስለ ጥርሱ ነጻ ይልቀቀው። ስለ ንብረት የተሰጠ ትእዛዝ 28 “በሬ ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው። 29 ነገር ግን በሬው አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ለባለቤቱ አስጠንቅቀውት ባይጠብቀውና ወንድን ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል። 30 ካሳ እንዲከፍል ቢወሰንበት ግን፥ የነፍሱን ካሳ የወሰኑበትን ያህል ይስጥ። 31 ወንድን ልጅ ቢወጋ ወይም ሴትን ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት። 32 በሬው ወንድ ባርያ ወይም ሴት ባርያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታው ይስጥ፥ በሬው ግን ይወገር። 33 አንድ ሰው ጉድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጉድጓድ ቢቆፍር ሳይከድነው ቢቀርና በሬ ወይም አህያ ቢወድቅበት፥ 34 የጉድጓዱ ባለቤት ዋጋውን ለባለቤቱ ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን። 35 የአንድ ሰው በሬ የሌላውን በሬ ቢወጋ፥ ቢሞትም፥ በሕይወት ያለውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም እኩል ይካፈሉት፤ የሞተውንም ደግሞ እኩል ይካፈሉ። 36 በሬው አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው። 37 “አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፥ ቢያርደው ወይም ቢሸጠው፥ በበሬው ፈንታ አምስት በሬዎች፥ በበጉም ፈንታ አራት በጎች ይክፈል።” |