Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፀአት 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


እስራኤላውያን ሲና ተራራ እንደ ደረሱ

1 የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።

2 ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ።

3 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ወጣ፤ ጌታም ከተራራው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር፦

4 በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንዴት እንደ ተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።

5 አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤

6 የካህናት መንግስት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።”

7 ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ ጌታ ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ።

8 ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት ሆነው፦ “ጌታ ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ ጌታ አደረሰ።


የሕዝቡ መቀደስ

9 ጌታም ሙሴን፦ “ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙና ለዘለዓለም እንዲያምኑህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣለሁ” አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለጌታ ነገረ።

10 ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገን ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤

11 በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ እያዩ ጌታ በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና።

12 ለሕዝቡም በዙሪያው ወሰን አድርግላቸው፥ እንዲህም በላቸው ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውን የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤

13 የማንም እጅ አይንካው፤ የሚነካው ግን በድንጋይ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳም ቢሆን፥ ሰውም ቢሆን አይድንም።’ ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ።”

14 ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ።

15 ሕዝቡንም፦ “ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴትም አትቅረቡ” አላቸው።

16 እንዲህም ሆነ በሦስተኛው ቀን ማለዳ ነጎድጓድ፥ መብረቅና ከባድ ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩ የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።

17 ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ በተራራው እግርጌ ቆሙ።

18 ጌታ በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ጢሱም ከእቶን እንደሚወጣ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ተናወጠ።

19 የቀንደ መለከቱ ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።

20 ጌታ በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ ጌታ ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።

21 ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ውረድ፥ ጌታን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉና ከእነርሱም ብዙዎቹ እንዳይጠፉ ሕዝቡን አስጠንቅቃቸው፤

22 ወደ ጌታ የሚቀርቡት ካህናትም ራሳቸውን ይቀድሱ ካልሆነ ግን ጌታ ያጠፋቸዋል።”

23 ሙሴም ጌታን፦ “አንተ በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፥ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ሊወጡ አይችሉም” አለው።

24 ጌታም፦ “ሂድ፥ ውረድ፤ አሮንንም ከአንተ ጋር ይዘህ ና፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እንዳያጠፋቸው ወደ ጌታ ለመውጣት አይተላለፉ” አለው።

25 ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደና ይህንን ነገራቸው።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos