ዘፀአት 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገርው፦ 2 “ማሕፀንን የሚከፈት በኩርን ሁሉ፤ በእስራኤል ልጆች መካከል፥ ከሰውም፥ ከእንስሳም ለእኔ ቀድስልኝ፥ የእኔ ነው።” የቂጣ በዓል 3 ሙሴም ሕዝቡን አለ፦ ከባርነት ቤት ከግብጽ የወጣችሁበትን ይህንን ቀን አስቡ፥ ጌታ ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። 4 እናንተ ዛሬ በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5 ጌታም ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኬጢያውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ኤዊያውያን፥ ወደ ኢያቡሳውያንም ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር ባገባህ ጊዜ ይህችን አገልግሎት በዚህ ወር ታገለግላለህ። 6 ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ለጌታ በዓል ይሆናል። 7 ሰባት ቀንም ሙሉ ያልቦካ ቂጣ ትበላለህ፥ በአንተም ዘንድ እርሾ ያለበት አይታይ፥ በድንበርህም ሁሉ እርሾ አይታይ። 8 በዚያም ቀን፦ “ከግብጽ በወጣሁ ጊዜ ጌታ ስላደረገልኝ ነው” ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። 9 በእጅህ እንደ ምልክት በዐይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ፥ የጌታ ሕግ በአፍህ እንዲሆን፥ ጌታ በብርቱ እጅ ከግብጽ አውጥቶሃልና። 10 በተወሰነለት ጊዜ ከዓመት ወደ ዓመት ይህችን ሥርዓት ጠብቃት። የበኩር ልጅ መቀደስ 11 ጌታ ለአንተና ለአባቶችህም እንደማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር ያመጣሃል ለአንተም ይሰጥሃል፤ 12 ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለጌታ ስጥ፥ የአንተ ከሆነ ከከብት ሁሉ ተባት ሆኖ አስቀድሞ የተወለደው ለጌታ ይሆናል። 13 የአህያውን በኩር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ፤ የሰውንም በኩር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። 14 እንዲህም ይሆናል በሚመጣው ጊዜ ልጅህ፦ ይህ ምንድነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ ጌታ በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብጽ አወጣን፤ 15 ፈርዖን እንዳይለቀን ልቡን ባጸና ጊዜ ጌታ ከሰው በኩር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኩር ድረስ በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለጌታ እሠዋለሁ፥ ነገር ግን የልጆቼን በኩር ሁሉ እዋጃለሁ። 16 ጌታ በብርቱ እጅ ከግብጽ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዐይኖችህም መካከል እንደ ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ። የደመና ዓምድና የእሳት ዓምድ 17 እንዲህም ሆነ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ምንም እንኳን ቅርብ ቢሆን በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፦ “ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብጽም እንዳይመለስ” ብሏልና። 18 ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ዞረው በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መንገድ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ምድር ለጦርነት ተሰልፈው ወጡ። 19 ሙሴም የዮሴፍን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ “በእርግጥ እግዚአብሔር ይጎበኛችኋል፥ አጥንቶቼንም ከዚህ ከእናንተ ጋር ውሰዱት” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና። 20 ከሱኮትም ወጡ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። 21 በቀንና በሌሊትም እንዲጓዙ፥ ጌታ ቀን በደመና ዓምድ መንገድ ሊመራቸው፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ ሊያበራላቸው ከፊታቸው ይሄድ ነበር። 22 የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ አልተለየም። |