መክብብ 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ጻድቃንና ጠቢባን፥ ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፥ ፍቅርም ሆነ ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም፤ ሁሉም በፊታቸው ነው። 2 የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፤ መልካሙ ሰው እንደ ኃጢአተኛው፥ የሚምለው ሰው መሐላን እንደሚፈራው ነው። 3 ለሁሉም አንድ ዓይነት ዕጣ ክፍል መኖሩ ከፀሐይ በታች በሚደረገው ነገር በሙሉ ይህ ክፉ ነው፥ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ በክፋት ተሞልታለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ውስጥ ይኖራል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። 4 ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። 5 ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፥ ሙታን ግን አንዳችም ነገር አያውቁም፥ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። 6 ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ከወዲሁ ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘለዓለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። 7 እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። 8 ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፥ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። 9 በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። 10 አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። 11 እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ፍልምያ ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ሀብትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፥ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። 12 ሰውም ጊዜውን አያውቅም፥ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ። 13 ከፀሐይ በታችም ይህን ጥበብ አየሁ፥ እርሷም በእኔ ዘንድ ታላቅ መሰለችኝ። 14 ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፥ ታላቅ ንጉሥም መጣባት ከበባትም፥ ታላቅ ግንብም ሠራባት። 15 ጠቢብ ድሀ ሰውም ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፥ ያን ድሀ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። 16 እኔም፦ ከኃይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፥ የድሀው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም አልሁ። 17 በሰነፎች መካከል ከሚጮኽ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። 18 ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፥ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል። |