Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


አሞጽ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የኤዶምያስን ንጉሥ ዐፅም አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎአልና ስለ ሦስት የሞዓብ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።

2 በሞዓብ ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የቂርዮትንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፤ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ መካከል ይሞታል፤

3 ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥” ይላል ጌታ።


በይሁዳ ላይ የተደረገ ፍርድ

4 ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የጌታን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉአቸው ሐሰቶቻቸው አስተዋቸዋልና ስለ ሦስት የይሁዳ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።

5 በይሁዳ ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።”


በእስራኤል ላይ የተደረገ ፍርድ

6 ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጻድቁን ስለ ብር፥ ችግረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሸጠዋልና ስለ ሦስት የእስራኤል ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።

7 የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፤ ቅዱሱንም ስሜን ለማርከስ አባትና ልጅ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤

8 በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፤ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ።

9 “እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ባሉጥ ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው ደመሰስሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ።

10 እኔም ከግብጽም ምድር አወጣኋችሁ፥ የአሞራዊውንም ምድር እንድትወርሱ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ።

11 ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጉልማሶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህ በእውነት እንደዚህ አይደለምን?” ይላል ጌታ።

12 እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችሁ፤ ነቢያቱንም፦ ትንቢትን አትናገሩ፥ ብላችሁ አዘዛችሁ።

13 “እነሆ፥ እህል የተሞላ ሠረገላ እንደሚያደቅቅ፥ እንዲሁም እኔ በመሬታችሁ ላይ አደቅቃችኋለሁ።

14 ፈጣኑ ሯጭ መሸሽ ሳይችል ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፤

15 ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም ሯጭ አያመልጥም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤

16 በዚያ ቀን በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥” ይላል ጌታ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos