3 ዮሐንስ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሰላምታ 1 ሽማግሌው፥ በእውነት ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ። 2 ወዳጄ ሆይ! በመንፈስ እንዳደግህ ሁሉ፥ በነገር ሁሉ እንዲሳካልህና በመልካም ጤንነት እንድትኖር እጸልያለሁ። 3 ወንድሞች መጥተው በአንተ ስላለው እውነትና አንተም በእውነት እንደምትመላለስ ሲመሰክሩልኝ እጅግ ደስ አለኝ። 4 ልጆቼ በእውነት እንደሚመላለሱ ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም። የጋይዮስ መመስገን 5 ወዳጄ ሆይ! ምንም እንኳ እንግዶች ቢሆኑም ለወንድሞች የምታደርገውን ነገር ሁሉ በታማኝነት ታደርጋለህ፤ 6 እነርሱም በቤተ ክርስቲያን ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳቸው መልካም ታደርጋለህ፤ 7 ስለ ስሙ ብለው፥ ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ ወጥተዋልና። 8 ስለዚህ የእውነት የሥራ ተባባሪዎች እንድንሆን እንደነዚህ ያሉትን ልንቀበል ይገባናል። ዲዮጥራፊስና ድሜጥሮስ 9 ለቤተ ክርስቲያን አንድ ነገር ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ ለመሆን የሚፈልገው ዲዮጥራፊስ አልተቀበለንም። 10 ስለዚህ እኔ ከመጣሁ፥ ስለ እኛ የተናገረውን ክፉ ቃል፥ የሠራውን ሥራ አሳስበዋለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሉአቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፥ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል። 11 ወዳጄ ሆይ! መልካሙን እንጂ ክፉን አትምሰል። መልካም የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። 12 ድሜጥሮስ በሁሉም ተመስክሮለታል፤ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም እንመሰክርለታለን፤ ምስክርነታችን ደግሞ እውነት እንደሆነ ታውቃለህ። የመጨረሻ ሰላምታ 13 የምጽፈው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ነገር ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወደድሁም፤ 14 ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ፊት ለፊት እንነጋገራለን። 15 ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላም ይሉሃል። ወዳጆችን በየስማቸው ሰላም በልልኝ። |